የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የ6 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት የሀገራችንን ሉኣላዊነት ለማስከበር ሁሉም የክልሉ ህዝቦች አኩሪ ተግባር መፈጸማቸውን አስታውቀዋል ።
የክልሉ የጸጥታ ሃይል ከመከላከያ ጎን ተሰልፎ የሀገር ሉኣላዊነት ማስከበር ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ህዝብ ሀገሩን ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ለመጠበቅ ልጆቹን ግንባር ድረስ ከመላክ ባሻገር በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወቁት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅና የግጭት አካባቢዎችን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል ።
በተለይም በእነዚህ አካባቢዎች የተካሄደ የሰላም ውይይቶችና ኮንፈረንሶች እንዲሁም የእርቀ ሰላም መድረኮች የተሻለ ሰላም ማምጣታቸውን አቶ እርስቱ ገልጸዋል ።
በየጊዜው ለሚፈጠሩ ግጭቶች ተጠያቂ የሆኑትን ህግ የማቅረብና አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረግ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉም አስታውቀዋል ።
በሌላ በኩልም በክልሉ በያዝነው የበጋ ወቅት 204 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የለማ ሲሆን ÷ከዚህ ውስጥ 5 ሺህ 100 የሚሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንደሆነ በሪፖርታቸው አመልክተዋል ።
በክልሉ በቀጣዮቹ የበልግና መኸር ወቅት የግብርና ስራዎች የኩታ ገጠም አሰራር፣የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የሜካናይዜችን አመራረትን ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል ።
በልዩ ልዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ በመምከር ማጽደቅ እንዲሁም ሹመት እና ረቂቅ ቃለ ጉባኤ ላይ በመምከር የምክር ቤቱ አባላት ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!