Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ የድርጅቱን መደበኛ ስብሰባ በባሕር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጣሂር መሐመድ ስብሰባውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ በስብሰባው ያለፉት ጊዜያት የፓርቲው እንቅስቃሴ ይዳሰሳል፤ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎችም እንደሚቀመጡ አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ አሁን ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አብን ለሕዝቡ ሊያበረክት ስለሚችለው አስተዋጽኦ፣ በቅርቡ በሚደረገው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ላይ፣ 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ምን ይመስል እንደነበር እና በሂደቱ የአብን ሚና ምን እንደነበር በስፋት ተነስቶ ጥልቅ ውይይት ይደረግበታል ነው ያሉት።

አቶ ጣሂር እንዳሉት፥ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ጦርነት በመቀልበስ ሂደት የአብን ድርሻ እንዴት እንደነበር በስፋት ይፈተሻል፤ የሕልውና ዘመቻው የተመራበት ሀገራዊ ሁኔታን በመገምገም ቀጣይ ሊከናወኑ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ይመክራል ብለዋል።

ሁሉን አቀፍ እና አካታች ሀገራዊ መግባባትን በተመለከተ አብን በተለይ የአማራ ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልባቸውን ጉዳዮችም ይዳስሳልም ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በድርጅቱ ቀጣይ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅም ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ሰብሰባ ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ በስፋት የሚተነተን ሲሆን÷ የድርጅቱን የአሠራር ሥርዓቶች በመከተል በኩል መስተካከል ያለባቸውን ክፍተቶች በሚመለከትም ይመክራል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.