Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ እና ለመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው የህንድ ባለሀብቶች እና ከህንድ የኢንቨስትመንት ፎረም አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ያልነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ክፍት ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

የሕንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅትም መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መልካም አብነት መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ህንዳውያን ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ከፀጥታ እና ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን÷ ከባለሀብቶቹ ለተነሱት ጥያቄዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደ ሀገር ለሁሉም ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ አምባሳደር ሬድዋን አረጋግጠዋል፡፡

ህንዳውያን ባለሀብቶች በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት መፍታት ከቻለች በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አህጉር ትልቋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን አቅም አላት ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከባለሀብቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ጊዜ ሰጥቶ በማዳመጥ ለክፍተቶች እልባት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት በመረዳታቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ ከ6 መቶ በላይ የህንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.