የንግዱ ማህበረሰብ የበዛ ትርፍ ከመፈለግ ይልቅ የችግር ጊዜን ተባብሮ እንዲያሳልፍ የሃይማኖት አባቶች ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የንግዱ ማህበረሰብ ብዙ ትርፍ ከመፈለግ ይልቅ የችግር ጊዜን ተባብሮ ማለፍ ላይ ማተኮር እንዳለበት የሃይማኖት አባቶች ጠየቁ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ አላግባብ የዋጋ ጭማሪዎች በመሰረታዊ ፍጆታዎችና በሌሎች እቃዎች ላይ ታይቷል።
የዋጋ ጭማሪን የሚያባብሰው የንግዱ ማህበረሰብ ትልቅ ትርፍ መሻትና ሸቀጦችን መደበቅ ሲሆን ፥ ማሳያውም ሰሞኑን ከምግብ ዘይት ዋጋ ማሻቀብ ጋር ተያይዞ መንግስት ባደረገው ፍተሻ በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ ተገኝቷል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶች እንዳሉት ፥ እነዚህ ተግባራት በዓለማዊም ይሁን በሃይማኖታዊ ዘንድ የተወገዙ ናቸው።
”ያለ ምክንያት የሸቀጦችን ዋጋ መጨመርና ደብቆ ሕዝብ እንዲቸገር ማድረግ የሃይማኖት አስተምህሮን የሚቃረንና ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር ነው” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ ፥ በሕብረተሰቡ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል።
በየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ የሚጠቀሱት ርህራሄ፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ በጎነትና አንድነት መሆናቸውን ጠቅሰው ፥ የሃይማኖት አባቶች በትክክለኛው መንገድ ሰርተው ራሳቸውን እንዲጠቀሙና ሌላውንም እንዲጠቅሙ የሚያዙ ናቸው ብለዋል።
አያይዘውም አንዱ በሌላው ላይ እንዲጨክን የሚያዝ የእምነት ተቋም እንደሌለ አመላክተው ፥ የንግዱ ማህበረሰብም ሕዝቡን ጫና ውስጥ ከመክተት ይልቅ “ከእኔነት” ወጥቶ “እኛ” ወደ ማለት መሄድ አለበት ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼህ ሓሚድ ሙሳ በበኩላቸው፥ በየጊዜው የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ከራስ ወዳድነት፣ ከስግብግብነትና ፈጣሪን ካለመፍራት የሚመነጩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ መሸጥ፣ መለወጥና ነግዶ ማትረፍ ሕጋዊ ቢሆንም አላግባብ ለማትረፍ መሞከር ግን ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን የሚጥስ ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ከሚጨምሩና ምርቱን ከሚደብቁት ባሻገር በትክክለኛው መንገድ የሚሰሩት ሊመሰገኑ ይገባል ይህም ፈጣሪ የሚወደው ተግባር መሆኑን የሃይማኖት አባቶቹ አክለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!