Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ከ13 ሺህ በላይ ደረጃዎች ቢወጡም ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር ክፍተቶች መኖራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከ13ሺህ በላይ ደረጃዎች ቢወጡም አምራቾች ፣ አገልግሎት ሰጪዎችና ተጠቃሚዎች ደረጃዎችን በሚፈለገው ልክ ከመተግበርና ጥቅም ላይ ከማዋል አንፃር ክፍተቶች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት በቀለ ገለጹ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በምርትና በአገልግሎቶች ላይ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ ደረጃዎችን አውጥቶ እንዲተገበሩ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት በቀለ ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ ይህን የገለጹት በምስራቅ ኢትዮጵያ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቆዳ ጥራትና ደረጃዎች ዙሪያ በድሬዳዋ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።

የኢትዮጵያ ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቀና በዓለም አቀፍ ገበያ በጥራት ተወዳዳሪ ሆነው የሚፈለገውን የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት እንዲችሉ ደረጃዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ዶክተር መሠረት አስገንዝበዋል።

ደረጃዎች የውጪ ገበያን በማሣለጥ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ሁሉም ለደረጃዎች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳሰበዋል።

ኢትዮጵያን በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተሰማሚ የሆነ የአየር ንብረት ቢኖራትም ፥ በምርትና አሽጐ በመላክ ባለው ሂደት ከሚፈለገው ደረጃ በታች በመሆናቸው ከዘርፉ ማግኘት የሚገባን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ በመድረኩ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል የሃገሪቱን ዓመታዊ አጠቃላይ ምርት 12 በመቶ የሚሸፍነው ቆዳና ሌጦ ቢሆንም በምርት ጥራት ጉድለት ሳቢያ ተገቢውን የውጪ ምንዛሬ እየተገኘ ባለመሆኑ ለጥራት ደረጃዎች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በምክክር መድረኩ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቆዳ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች፣ ላኪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፈ ሆነዋል።

በተሾመ ኃይሉ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.