Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 5ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ውሳኔውም እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ (2014-2018) ሰነድ ላይ ሲሆን የመጀመሪያውና በ2008 የተዘጋጀው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ በ2013 በጀት ዓመት ተጠናቋል፡፡ በመሆኑም በፋይናንስ ዘርፍ የተካሄዱ ለውጦችንና የተከሰቱ አዳዲስ ዕድሎችን ለማስተናገድ፣ እንዲሁም ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና አቻ አገራት ከደረሱበት የፋይናንስ አካታችነት ደረጃ ለመድረስ ይቻል ዘንድ ሁለተኛው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ (ከ2014 እስከ 2018) ሁሉንም የባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የተዘጋጀ ረቂቅ ስትራቴጂ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በስትራቴጂ ሰነዱ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በመጀመሪያው ስትራቴጂ አፈጻጸም የተገኙና ሌሎችንም ስኬቶች የበለጠ ለማጎልበት አዳዲስ የተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችንም በመጠቀም በሚቀጥሉት አምስት አመታት የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ያለመ መሆኑን በማረጋገጥና ተጨማሪ ግብዓቶችን በማከል በሙሉ ደምጽ በማጽደቅ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ለገጠር የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም (ምዕራፍ III) ማስፈፀሚያ እንዲውል ከዓለምዐቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ጋር በተፈረመው የብድር ስምምነት ላይ ነው፡፡ የግብርና ልማት ስትራቴጂያችን የህዝቡን የማምረት አቅም በማጎልበትና ይህንኑ በሰፊው በመጠቀም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስትራቴጂው አርሶ አደሩ ከእጅ ወደ አፍ ከሚያመርትበት የኢኮኖሚ ሥርዓት ተላቆ ለገበያ ወደሚያመርትበት የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲሸጋገር ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ምርት ለማምረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችንና መሣሪያዎችን ለመግዛት፣ ካመረቱም በኃላ ወደገበያ ለማጓጓዝና ለመሸጥ፣ ለኑሮ የሚያስፈልገውን የፍጆታ ዕቃዎች ለመግዛትና ለመሳሰሉት ተግባራት በገጠር ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ሊኖር ይገባል፡፡ እነዚህን ተግባራት በተቀናጀና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር የሚያስችል ብር 245,000,000.00 (ሁለት መቶ አርባ አምስት ሚሊየን ብር) የብድር ስምምነት መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ብድሩ ከአገሪቱ የብድር ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ መሆኑን፣ ጥቅም ላይ ባልዋለው የብድሩ ገንዘብ ላይ ብቻ በዓመት እስከ 0.50% የሚደርስ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት እንዲሁም 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት መሆኑን በማረጋገጥ ምክር ቤቱ ስምምነቱ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለለፍ ወስኗል፡፡

3. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የፓስፊክ አገራት ድርጅት (አካፓድ) የተቋቋመበትን ስምምነት ባሻሻለው የጆርጅታውን ስምምነት ላይ ነው፡፡ የጆርጅታውን ስምምነት ዋነኛ ዓላማ በአባል አገራት ሕዝቦች መካከል የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የባህል ትስስር ለማጠናከር፣ የአባል አገራትን ህብረትና አንድነት ለማጎልበት እና አንድ በሚያደርጋቸው አለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ላይም በጋራ ለመስራት ብሎም ዘላቂ ልማት እና ድህነት ቅነሳን ለማሳካት ነው፡፡ አገራችን የድርጅቱ አባል መሆንዋ የሚያስገኘው ጠቀሜታ የላቀ በመሆኑ የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም ስምምነቱ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለለፍ ወስኗል፡፡

4. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፤ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለሚሰጡዋቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚከፈሉ ክፍያዎችን ለመወሰን ተዘጋጅተው በቀረቡ 4 (አራት) ረቂቅ ደንቦች ላይ ሲሆን የቀረቡትን የክፍያ ተመኖች ተመጣጣኝነት በማረጋገጥ እና ግብዓቶችን በመጨመር ያጸደቀ ሲሆን ደንቦቹ በነጋሪት ጋዜጣ ከታተሙበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል፡፡

5. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕን፣ ወንጂ/ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫ፣ ከሰም እና በለስ ስኳር ፋብሪካዎችን ለማቋቋም በቀረቡ 6 (ስድስት) ረቂቅ ደንቦች ላይ ሲሆን ስኳር ኮርፖሬሽን ላለፉት በርካታ ዓመታት ውስብስብ ችግሮች ያሉባቸውን የስኳር ፕሮጀክቶችና ፋብሪካዎች አንድ ላይ ሰብስቦ ሲመራ መቆየቱ ትኩረቱንና አቅሙን የበተነው በመሆኑ ተልዕኮውን በማሳካት ረገድ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ስለሆነም ለተቋሙ የተሰጡ ሰፊና ውስብስብ ተልዕኮዎችን መቀነስ እንዲሁም የስኳር ፋብሪካዎቹ ህጋዊ ሰውነት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ፋብሪካዎቹ ወደ ግልይዞታ እስከሚዛወሩ ድረስ አክሲዮናቸውን ሙሉ በሙሉ በመያዝ እንዲቋቋሙ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕን እና አምስቱን የስኳር ፋብሪካዎች ለማቋቋም የቀረቡትን ረቂቅ ደንቦች ያጸደቀ ሲሆን ደንቦቹ በነጋሪት ጋዜጣ ከታተሙበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል፡፡

6. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተመለከተው የቱርክ ሪፐብሊክ ጋር የተደረጉ ወታደራዊ የትብብር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ቱርክና ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ጥብቅ ወዳጅነት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ቱርክ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን አጋር መሆኗን በተደጋጋሚ ያረጋገጠች አገር ናት፡፡ በዚህ መነሻነትም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በቱርክ አንካራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቀት ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓም የተፈረሙ ሶስት ስምምነቶች ለምክር ቤቱ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከስምምነቶቹ አላማ በትምህርትና ስልጠና፣ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪ ግንባታ፣ የሳይበር ጥቃት መከላከል፣ በሰላም ማስከበር፣ የወታደራዊ ፋይናንስ ትብብር፣ በባህር ላይ ዉንብድና መከላከል ላይ በሚደረጉ ዘመቻዎች ለመተባበር የሚያስችል ማዕቀፍ መፍጠር ነው፡፡ ምክር ቤቱም በቀረቡት ሶስት የሁለትዮሽ ስምምምነቶች ላይ በመወያየት ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.