Fana: At a Speed of Life!

በቅርቡ የተሾሙ አምባሳደሮች የ100 ቀናት የስራ እቅዳቸውን አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ ሹመት የተሰጣቸው አምባሳደሮች በመጀመሪያዎቹ 3 ወራት የሚያከናውኗቸውን የስራ እቅድ ዛሬ አቅርበዋል።
 
አምባሳደሮቹ የ100 ቀናት እቅዶቻቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በተገኙበት ነው ያቀረቡት፡፡
 
የቀረቡት እቅዶችም አምባሳደሮቹ ከተሰጣቸው ተልዕኮ አንፃር የሀገር ብሄራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ሂደት ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ናቸው በሚል በበጎ ጎኑ ታይተዋል።
 
አምባሳደሮቹ እንደየተመደቡበት አካባቢ ያሉ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታና ፍላጎት አኳያ በተሻለ መልኩ ሊታዩ ይገባሉ የተባሉ ሀሳቦች በእቅዶቹ እንዲካተቱ አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
 
አቶ ደመቀ መኮንን አምባሳደሮቹ የተመደቡባቸውን ሀገራት ማህደር እና አሰላለፋቸውን በሚገባ በመረዳት የኢትዮጵያን ፍላጎት ያገናዘበ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
 
በባለ ብዙ ወገን ግኑኝነትም የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ ግኑኝነትን አስቀድሞ በመለየት ሀገራዊ ተልዕኮን በብቃት መወጣት እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.