ሚኒስቴሩ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አባዎራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ወደ ስራ ማስግባቱን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ከዓለም ባንክ በረዥም ጊዜ ብድር በተገኘ ገንዘብ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አባዎራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ወደ ስራ አስገብቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ፕሮጀክቱ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ስራ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን፣ ሴቶችን እና ስራ አጥ ወጣቶችን በእንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ላይ በማሰማራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በአለም ባንክ የሚደገፈው የእንስሳት አና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት፥ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ከባንኩ በረጅም ጊዜ በተገኘ 170 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እና ከመንግስት በተመደበ 190 ሚሊየን ብር የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት በአራት ዘርፎች ለደህነት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በእነዚህ ዘርፎች ለማሳተፍ እየተመለመሉ ያሉት እና የተለዩት የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ሴቶች እና ስራ አጥ ወጣቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በስድስት ክልሎች በ58 ወረዳዎች በ1 ሺህ 755 ቀበሌዎች የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት፥በሶስት እርከን የሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮች የሚሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል።
የመጀመርያው እርከን ሴቶች እና ስራ አጥ ወጣቶች እየተደራጁበት ያለው ሲሆን፥ ሁለተኛው እርከን የገበሬ ማህበራት፣ ሶስተኛው እርከን ደግሞ የህብረት ስራ ማህበራት ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ደረጃ ጉደታ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ባሉ 23 ወረዳዎች ፕሮጀክቱ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ፕሮጀክቱ የታሰበለተን አላማ ያሳካ ዘንድ እንደ ክልል አሁን የተጀመሩትን የስራ ቦታዎች ግንባታ ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።
የአማራ ክልል አለም ባንክ የሚደገፈው የእንስሳት አና አሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙሉቀን ዘሪሁን በበኩላቸው፥ እስካሁን ከ24 ሺህ በላይ በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ የቡድን አባላት መደራጀታቸውን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ብሄራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት ደግሞ ፕሮጀክቱን በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በስላባት ማናዬ