መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በመደበቅ በተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት የመረጃ ጥናትና ክትትል በማድረግ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ ከፌዴራል፣ ከአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም ሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የተቀናጀ ዘመቻ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በመደበቅ በተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡
የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፥ ከመንግሥት የተሰጣቸውን ህጋዊ የአስመጭነት እና የአከፋፋይነት ፈቃድ እንደ ሽፋን በመጠቀም የዋጋ ንረትንና የኢኮኖሚ አሻጥርን በሚፈጥሩ የንግድ ድርጅቶች ላይ ጥብቅና ተከታታይ የመረጃ ጥናትና ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ፣ በሰበታ እንዲሁም በአዳማ ከተማና አካባቢው የምግብ ሸቀጦች የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ምስር እና ቦሎቄ በተለያየ ሽፋን ማለትም በመጋዝን እና በመኖሪያ ቤት ዉስጥ በማከማቸትና በመደበቅ የተገኙ 25 ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል፡፡
ለአብነትም በአዳማ ከተማ ስራ ባቆመው የረር ዱቄት ፋብሪካ በተባለ መጋዝን ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር ተደብቆ ተገኝቷል ነው ያለው፡፡
በዚህ የተቀናጀ ዘመቻ እስካሁን በተደረገው ቆጠራ መሰረት ከ912 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር፣ ከ49 ሺህ 500 በላይ ኩንታል ሩዝ፣ ከ3 ሺህ 449 ኩንታል በላይ ዱቄት፣ 11 ሺህ ኩንታል ምስር፣ 4 ሺህ 700 ኩንታል ቦሎቄ እና ከ2 ሺህ ኩንታል በላይ ባቄላ እና ሌሎች የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶች ከተጠርጣሪዎች ጋር ተይዘዋል፡፡
በዚህ ሂደት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮችና ባለሙያዎች መተባበር ሲገባቸው የተለያየ ምክንያት በማቅረብ፣ ስልክ ዘግቶ በመጥፋትና ለህገወጦች ሽፋን በመስጠት እየተወሰደ ያለውን በጥናት ላይ የተመሰረተ ዘመቻ ለማደናቀፍ ጥረት ማድረጋቸውንም አስታውቋል።
ከእነዚህ መካከል 6 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለጊዜው የተሰወሩ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለው የዋጋ ጭማሪ ሕብረተሰቡን በኑሮ ውድነት እንዲማረር ለማድረግ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን ተከትለው በማይሰሩ፣ የቀረጥ ነፃ መብትን ተጠቅመው በሚያጭበረብሩና ምርት በህገወጥ መንገድ በመጋዝን በመደበቅ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ንረት እንዲከሰት በሚያደርጉ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ የመረጃ ክትትሉን አጠናክሮ መቀጠሉን ያስታወቀው የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት፥ በጥናት ላይ ተመስርቱ እያካሄደ ያለውን የዚህን ዘመቻ ውጤት በቀጣይም ለሕብረተሰቡ ይፋ እንደሚያደርግ ነው የገለጸው።
ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገው ጥረትም ህብረተሰቡ ላደረገው ላቅ ያለ ትብብር ምስጋና ያቀረበው አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በቀጣያም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!