Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ሲያካሂድ የነበረውን ጉባኤ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች፣ የ18 ዳኞችና ሶስት የካቢኔ አባላት ሹመት በማጽደቅ ተጠናቋል።

ለሁለት ቀናት በተለያዩ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ሲመክር የቆየው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ፥ የተለያዩ አዋጆች እና ደንቦች ላይ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ አፅድቋል።

በዚኅም በጉባኤው በስነምግባር እና በአቅም ውስንነት ስድስት የወረዳና የዞን ዳኞችን በማሰናበት ሶስት ዳኞች ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ የተደረገ ሲሆን÷18 የወረዳና የዞን ዳኞች ሹመትንና ሶስት የካቢኔ አባላት ሹመት ጸድቋል፡፡

የተሻሻለው የክልሉ አስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ÷ የተሻሻለው የክልሉ ዳኞች አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ÷ የተሻሻለው የክልሉ ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ስልጣንና ተግባርእንደገና ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጆች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የተሻሻለው የክልሉ ጤና አገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅና የተሻሻለው የክልሉ ኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ቀርቦ የምክር ቤቱ አባላት በአዋጆቹ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ መርምረው አጽድቀዋል፡፡

በጉባኤው ሶስት የካቢኔ አባላት ሹመት የጸደቀ ሲሆን በዚህም መሠረት አቶ ኡቦንግ ኡጉታ የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ቻንኮት ቾል የክልሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ኃላፊ፣ ወይዘሮ ኡላንግ ጋችን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ በማድረግ ሹመታቸውን ማፅደቁን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.