የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያውያን ኤች አር 6600ና ኤስ 3199 የተባሉት አደገኛ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ ሰፊ ዘመቻ እንዲያደርጉ አቶ ደመቀ ጥሪ አቀረቡ

By Mekoya Hailemariam

March 22, 2022

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላው አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ወገኖች በአሜሪካ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ላይ ለማሳለፍ የታቀዱት እጅግ አደገኛ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ ከፍተኛ ዘመቻ እንዲያደርጉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮነን ጥሪ አቀረቡ።

አቶ ደመቀ በመላው አሜሪካ ከሚገኙ የኮሚዩኒቲ አደረጃጀት ኃላፊዎች፣ የታስክ ፎርስ፣ የሲቪክ ማህበራት አመራሮችና ተወካዮች ጋር ትናንት በዙም ውይይት አድርገዋል።

በአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት በኩል በረቂቅ ደረጃ የሚገኙት ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 በሚል የቀረቡ ረቂቅ ህጎች ኢትዮጵያውያን በደም መስዕዋትነት ያስከበሩትን ሉዓላዊነት በእጅ አዙር ለመቀማት የተሸረቡ ሴራዎች ናቸው ብለዋል።

ረቂቅ ህጎቹ ከጸደቁ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖራት የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት በሌሎች ኃይሎች በጎ ፈቃድ እንዲንጠለጠልና ራሷን የማትከላከል ሽባ አገር የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ወገናችን ጨምሮ ዳያስፖራውን ከእናት አገሩ እና ዘመዱ ጋር የሚያቆራርጡ እጅግ አሳሪ እና ታይቶ የማይታወቅ የሉዓላዊነት መቀሚያ ረቂቅ ህጎች ናቸውም ነው ያሉት።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል አገራችን ገጥሟት የነበረውን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና ለመቋቋም ዳያስፖራው ወገናችን ቁር እና ጸሃይ ሳይገታው ላሳየው እውነተኛ አገር ወዳድነት ምስጋና ያቀረቡት አቶ ደመቀ፥ አነዚህ ረቂቅ ህጎችም እንዳይጸድቁ ከምንጊዜውም በላይ በተቀናጀ የአንደነት ዘመቻ እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል።

መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች አገርን ያስቀደሙ እና ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ታሳቢ በማድረግ የሚወሰኑ መሆናቸውን ጠቁመው በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ መቼም ቢሆን እንደማይደራደር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያለትን ረጀም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዲጠናከር ሁሌም ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ሉዓላዊነቷን የሚጋፉ የእጅ አዙር ጥምዘዛዎችን ግን እንደማትቀበል ነው ያረጋገጡት።

አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው ዳያስፖራው በየአካባቢው ያሉ የመንግስት ተመራጮችን በስልክ፣ በኢሜል፣ ፊርማ በማሰባሰብና በአካል እያገኘ የረቂቅ ህጎቹን አፍራሽነት እንዲያስረዳ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎችም ረቂቅ ህጎቹ የመንግስትና የፓርቲ ሳይሆኑ የአገርን አንድነትና ቀጣይነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ከምንጊዜውም በላይ በቅንጅት በመስራት ባሉበት እንዲመክኑ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።