የጣሊያኑ መከላከያ ሚኒስትር የካቲት 12 ኢትዮጵያውያን የተጨፈጨፉባቸውን ስፍራዎች ሊጎበኙ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የጣሊያኑ መከላከያ ሚኒስትር ሎሬንዞ ጉኤሪኒ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ወታደሮች የተጨፈጨፉባቸውን ስፍራዎች እንደሚጎበኙ ገለፁ።
በደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ የሚያሳይ መፅሃፍ በፓውሎ ቦርሶስ ተመርቋል።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሩ ሀገራቸው ለተሳተፈችባቸው ታሪካዊ ሁነቶች ሀላፊነት አለባት ብለዋል።
አያይዘውም በጣሊያን ጦር ጭፍጨፋ የተፈፀመበትን ስፍራ እንደሚጎበኙ ይፋ ማድረጋቸውን አንሳ የተባለው የዜና አውታር ዘግቧል ።
የካቲት 12 ቀን 19 29 ዓ.ም በኔፕልስ ጣሊያን ልዕልት መወለዷን አስመልክቶ የጣሊያን መንግስት የኢትዮጵያ አገረ ገዢ የነበረው ፊልድ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ በቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ደስታውን ለመግለጽ ግብዣ ጠርቶ ነበር።
በወቅቱም የጣሊያንን አገዛዝ የተቃወሙት አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በወረወሩት ቦምብ ግራዚያኒን ጨምሮ በርካታ የጣሊያን ባለስልጣናት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህን ተከትሎም በግራዚያኒ ትዕዛዝ በአዲስ አበባ እና በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መጨፍጨፋቸው የሚታወስ ነው።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision