Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ሊገነባ ነው።
በድሬዳዋ በኩላሊት ህመም ምክንያት ለከፋ የጤና ችግር የሚዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ የአስተዳደሩ አመራሮች፣ ነዋሪዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በጎ-ፍቃደኛ ወጣቶች ብሎም በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ወገኖች ለማዕከሉ ግንባታ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ተብሏል፡፡
በዚህም በቅርብ ጊዜ 10 የኩላሊት እጥበት ማሽን ግዢ ተፈፅሞ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል ነው የተባለው።
ለዚህ አገልግሎት የሚውል የኩላሊት እጥበት ማዕከል ግንባታ በናሽናል ሲሜንት አክሲዮን ማህበር ሙሉ ወጪ በድሬዳዋ ሳቢያን ሆስፒታል ለመገንባት የሚያስችል የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።
በመርሀ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፥ የማዕከል ግንባታው ጥራቱን በጠበቀና ለህብረተሰቡ ምቹ በሆነ አግባብ በሚቀጥሉት 45 ቀናት ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
በኩላሊት እጥበት ማሽን ግዢና ግንባታ ስራዎች ውስጥ ከመንግስት ምንም አይነት የገንዘብ ወጪ እንዳልተደረገም አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው፥ ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአስተዳደሩ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የናሽናል ሲሜንት አክሲዮን ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊና የዋና ስራ-አስፈፃሚው ተወካይ አቶ ወንዱ ንጉሴ፥ አክሲዮን ማህበሩ የስራው አንድ አካል አድርጎ ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች ውስጥ የማህበራዊ ልማት ተደራሽነት ስራዎች መሆናቸውንና በተለይም ፋብሪካው ባለበት የገጠር ቀበሌዎችና ለከተማ አስተዳደሩ ልማት ሰፋፊ ድጋፎች እያደረገ መሆኑን ከድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.