በመዲናዋ በቡድን በመደራጀት የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ 51 ተጠርጣሪዎች ተያዙ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቡድን በመደራጀት የተለያዩ ወንጀሎችን የፈፀሙ 51 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ የህዝብ መገልገያ በሆኑ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ እና ሿሿ የተሰኘውን የሌብነት ወንጀል በመደራጀት ሲፈፅሙ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል፡፡
በተለይም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የኃይል ማስተላለፊያ ኬብሎችን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ለልዩ ልዩ አገልግሎት የዘረጋቸውን ኬብሎች እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም ለጋራ መኖሪያ ቤቶች የኤሌትሪክ ኃይል ማስተላፊያ የተዘረጉ የኤሌትሪክ መስመሮች ላይ ትኩረት አድርገው ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ ገልፀዋል፡፡
ለቀላል ባቡሩ ከተዘረጉ ሃዲዶች ላይ ብሎኖችን እየፈቱ ሲወስዱ የነበሩ እና የባቡር ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ስርቆት ሲፈፅሙ የተገኙ 10 ወንጀል ፈፃሚዎችና የተሰረቀውን ንብረት የሚገዙ 4 ተጠርጣሪዎች ከተሰረቁት ንብረቶችና ወንጀሉን ለመፈፀም ሲገለገሉባቸው ከነበሩ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ጋር ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ባደረገው ጥረት የኢትዮ ቴሌኮም ፣ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ፣ የውሃና ፍሳሻ አገልግሎት እንዲሁም የቤቶች ልማት ካስገነባቸው 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተሰረቁ የኤሌትሪክ ገመዶችን እና ልዩ ልዩ ንብረቶችን ማስመለሱን ገልጿል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፥ ፖሊስ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እና የምርመራ ቡድን በማደራጀት ባከናወነው ተግባር በተለይ የተሰረቁ የባቡር መሰረተ ልማቶች የሚከማቹበት ቤት በቦሌ ክፍለ ከተማ እንደሚገኝ በመለየት እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ ከተያዙት ግለሰቦች በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው በከተማዋ በተለያዩ ስፍራዎች ተደራጅተው በተለምዶ ሿሿ የተባለውን የሌብነት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 27 ተጠርጣሪዎች እና ወንጀሉን ለመፈፀም ይጠቀሙባቸው የነበሩ 9 ተሽከርካሪዎች የተያዙ ሲሆን በተሽከርካሪ በመታገዝ የቅሚያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ግለሰቦች እና ወንጀሉን ለመፈፀም ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 5 ሞተር ብስክሌቶች እና 3 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ተይዘዋል፡፡
በተጠርጣሪዎቹ ከተቀሙ ንብረቶች መከከል 880 ሺህ ብር የዋጋ ግምት ያለው አይነቱ ቪትዝ የሆነ ተሽከርካሪን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሞባይል ስልኮችና ሌሎች የተለያዩ ኤግዚቢቶችን ማስመለስ ተችሏልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!