የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በአልጄሪያ ተገኘ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በአፍሪካዊቷ አልጀሪያ መገኘቱን የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አብደል ራህማን ቢን ቦዚድ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ ቫይረሱ ከጣሊያን በመጡ ሰዎች ወደ ሀገሪቱ መግባቱን ተናግረዋል።
የቫይረሱ ተጠቂ ከጥቂት ቀናት በፊት ከጣሊያን ወደ አልጀሪያ መግባቱንም አስታውሰዋል።
ግለሰቡ በአሁኑ ወቅትም በለይቶ ማቆያ ስፍራ ክትትል እየተደረገለት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ይህን ተከትሎም አልጄሪያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባት ሁለተኛው የአፍሪካ ሀገር ሆናለች፡፡
ግብጽ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባት የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር መሆኗ ይታወሳል።
በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁን ላይ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተስፋፋ ይገኛል።
በቻይና ብቻ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 715 ሲደርስ፥ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 78 ሺህ ከፍ ብሏል።
ምንጭ፡-ቢቢሲ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision