ከ82 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ሳምንት ከ82 ነጥብ 7ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል 76 ሚሊየን 535 ሺህ ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 6 ሚሊየን 178 ሺህ ብር የሚያወጡ የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ ድሬድዋ እና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ÷ በቅደም ተከተላቸው 22 ነጥብ 6 ሚሊየን፣ 21 ነጥብ 9 ሚሊየን እና 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዛቸው ተገልጿል ፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ነዳጅ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት፣ተሽከርካሪዎች፣የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣አደንዛዥ እጾች የግንባታ ብረት እና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ እና ጥቆማ መያዛቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!