Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷አሸባሪው ህወሓት ትልቅ እንቅፋት ቢሆንም በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ግን አሁንም ድረስ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል::

በህወሓት አሸባሪ ቡድን ምክንያት በየብስ ትራንስፖርት አማራጭ እርዳታዎችን ለክልሉ ተደራሽ ማድረግ ባለመቻሉ ከጥር ወር 2014 ጀምሮ በአየር ትራንስፖርት በበርካታ የደርሶ መልስ በረራዎች ሁሉ መድሃኒቶች እና አልሚ ምግቦችን እየደረሰ መሆኑን አንስተዋል::

በዚህ ሂደት ውስጥም መንግስት የፈጠራቸው ምቹ ሁኔታዎች ትልቅ ሚና መጫዎት እንደቻሉ ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት፡፡

በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ስርጭት ሂደት ላይ ህወሓት ትልቅ እንቅፋት ቢፈጥርም በመንግስት በኩል ግን በከፍተኛ ቁርጠኝነት ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ክልሎች እየገቡ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ÷ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የተረጂዎችን ቁጥር በማጥናት እንቅስቃሴ እየተደርገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምግብ እና ምግብ ነክ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግር እንደሌለ ጠቁመው ፤ ችግሩ ተደራሽነቱ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አቶ ምትኩ በተፈለገው መልኩ እርዳታውን ተደራሽ ለማድረግ አሸባሪው ህወሓት ትንኮሳውን ማቆም እና የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ መውጣት አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በአዲሱ ሙሉነህ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.