Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከሮክ ማዕከል አስተባባሪ እና ከሲቪ ፖል ሃላፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከሮክ ማዕከል አስተባባሪ ሙክተር ረመዳ እና በአውሮፓ የስደተኞችና የህዝብ ደህንነት ዘርፍ ማሻሻያ (ሲቪ ፖል) ሃላፊ ሰባስቲያን ሴፔርበር ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
ውይይቱ በአፍሪካ ቀንድ በህገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል ላይ የሚሳተፉ ቡድኖችን ግንኙነት መረብ ለመበጣጠስ እንዲያስችል በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ባሉ የህግ አስከባሪ አካላት መካከል የመረጃ ልውውጥ ለማሳለጥ እና የጋራ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ከኢጋድ፣ ከጂአይዜድ፣ ከዩኤን ኦ ዲሲ እና ከመሳሰሉት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም በወንጀል ድርጊት ተፈላጊዎችን ለፍትህ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ከሮክና ሲቪ ፖል ጋርም አብሮ የመስራትና የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረው የመቀጠል ስራ እንደሚከናወን ነው የገለጹት፡፡
 
ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑንም አብራርተዋል።
 
የሮክ ፕሮጀክትን በመጠቀም ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና በሰው የመነገድ ወንጀሎች የሚሳተፉ ቡድኖችን መረብ ለመበጣጠስ ብሎም የህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን ለመከላከል በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሀገራት ጋር እያደረገች ያለውን ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ሃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
 
አያይዘውም ኢትዮጵያ ለሮክ ፕሮጀክት ስኬታማነት በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ሀገሮች አንዷና ዋነኛ ሀገር ናት ብለዋል፡፡
 
ባለፈው ዓመት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በተሰራው ኦፕሬሽን የመረጃ ልውውጥ 80 በመቶ የተገኘው ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እንደሆነና ውጤታማ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
 
በቀጣይም መሰል ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት በመግለጽ ኮሚሽነር ጀኔራሉ ላደረጉላቸው አቀባበል እና መስተንግዶ ምስጋና ማቀረባቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
በቀጣይም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር አብሮ በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ኮሚሽነር ጀነራሉ አረጋግጠዋል።
 
ሮክ በአውሮፓ ህብረት የሚደገፍ ተቀማጭነቱን ሱዳን ካርቱም ያደረገ ፕሮጀክት ሲሆን÷ በአፍሪካ ቀንድ ጭምር የህግ አስከባሪዎች የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ የሚሰራና ዓላማው በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሰዎች የመነገድ ወንጀል ላይ የሚሳተፉ ቡድኖችን የወንጀል መረብ መበጣጠስና ስደተኞች በህገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎችን መቀነስና መከላከል ነው።
 
በዚሁ የትብብር ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አንድ ከፍተኛ መኮንን ተመድቦ እየሰራ እንደሚገኝም ታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.