Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ቱርክ የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም በአንካራ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱርክ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ኤምባሲ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሀገራችንን የወጪ ንግድ እና የኢንቨስትመንት እድል የሚያስተዋውቅ ፎረም በቱርክ አንካራ ተካሄደ።

በፎረሙ በቱርክ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ከ100 በላይ ባለሃብቶች እንዲሁም ከ25 በላይ የኢትዮጵያ የንግድ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ተሳትፈዋል።

የቱርክ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፈርዱን ሲቫሂሮግሉ በመክፈቻ ንግግራቸው፥ ኮንፌዴሬሽኑ ከ25 ሺህ በላይ ኩባንያዎች በአባልነት በማቀፍ በቱርክ የሚገኙ የሀገሪቱ ባለሃብቶችን ከተለያዩ ሀገራት ጋር በማገናኘት የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚሰራና መሆኑን ተናግረዋል።

በቱርክ መንግስት የሚደገፍ የሲቪክ ማህበር መሆኑን በመጠቆምም የዚህ አይነት ፎረም ከኤምባሲው ጋር በጋራ መዘጋጀቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን የበለጠ ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል ።

ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የኮንፌዴሬሽኑ በአዲስ አበባ ቢሮ እንደሚከፍት አስታውቀዋል።

በቱርክ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አደም መሀመድ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እና በቱርክ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት በማንሳት፥ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተደረገው ጉብኝት የዚህ መልካም ግንኙነት እድገት አይነተኛ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በፖለቲካው ዘርፍ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን በመግለጽ ስምምነቶቹን ወደ ተግባር ለመቀየር በትብብር መስራት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ምቹ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ለቱርክ ባለሃብቶች ጥሪ አቅርበዋል።

የሀገራችንን የገቢና ወጪ ምርቶች አስመልክቶ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ቦርድ አባል ዶ/ር አይናለም አባይነህ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ የወጪ ምርቶችን ወደ ቱርክ ገበያ ለማስገባት ለሚፈልጉ የቱርክ ባለሀብቶች ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እና በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የበለጠ ለማሻሻል እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በፎረሙ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ሴክሬታሪ ጀነራል አቶ ውቤ መንግስቱ ፥ በኢትዮጵያ በኩል ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.