Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል ህዝብን ህይወት ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ለጋሽ ድርጅቶች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ህዝብን ህይወት ለማሻሻል የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ዓለምአቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች አመራሮች ገለጹ፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አካላት ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችና አምባሳደሮች ጋር በሰብዓዊ ድጋፍና በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ላይ በሸቤሌ ዞን ጎዴ ከተማ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ዓላማ ህብረተሰቡን ከድርቅ ለመከላከል የተጀመሩት ልማታዊ እቅዶች በሚተገበርበትና የሶማሌ ክልላዊ መንግስት በድርቁ ምላሽ የወሰደውን እርምጃ እንዲሁም በክልሉ አሁን ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስፈልጉትን ስትራቴጂዎችና የህብረተሰቡ ኑሮ የሚሻሻልበትን ሁኔታዎች መለየት እንደሆነ ተገልጿል።

የህዝቡንና የእንስሳትን ህይወት ለመታደግ የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶ የመንግስት ሪፖርት ከቀረበ በኋላ የለጋሽ ድርጅቶች አመራር አካላት ለተፈጥሮ አደጋው አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን ገልጸው ፥ አሁን ላይ የክልሉን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል አጠቃላይ ትብብርና ደጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የድርቁ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ በኋላ የሚጠናቀቅ ቢሆንም የመንግስት እርምጃ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ሃላፊ ዶክተር ካትሪን ሶዚ የተመራ ልዑካን ቡድን በጎዴይ ከተማ ከዞኑና ከተማ አስተዳደር ከሀገረ ሽማግሌዎች ጋር ተወያይተዋል።

ልዑካን ቡድኑ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና የካናዳ አምባሳደር ስቴፋን ጆቢን ማካተቱን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሀመድ አብዲ አፌይና በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ማማዱ የሚመራ ልዑካን ቡድን ጋር በሶማሌ ክልል የሚገኙ ዓለምአቀፍ ስደተኞች መልሶ ማቋቋምና የስደተኞቹን ህይወት ሊቀይሩ በሚችሉ ፕሮጀክቶች ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.