ኤች አር-6600 እና ኤስ-3199 ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ እየተካሄደ ያለው ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ላይ የተዘጋጁት ኤች አር-6600 እና ኤስ-3199 ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ኃይል አስተባባሪ አቶ ጣሰው መላከህይወት ተናገሩ፡፡
አስተባባሪው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ÷ የኤስ-3199 ረቂቅ ለአሜሪካ ሴኔት ማለፍ መጽደቁን የሚያረጋግጥ ባለመሆኑ እንዳይጸድቅ ለማድረግ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአሜሪካ ምክር ቤቶች ሕግ የማጽደቅ አሰራር አንድ ረቂቅ ሕግ ሆኖ ከመጽደቁ በፊት በርካታ ሂደቶችን እንደሚያልፍ ማወቅ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ጣሰው፥ በዚህ መሰረት የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የተመራለትን ኤስ-3199 ሰነድ ተወያይቶ ማፅደቅ ቀጥሎም ረቂቁ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቆትና የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ፊርማ እንደሚጠብቅ አስረድተዋል።
በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ወደ ላይና ወደታች ምልልስ ሊኖርም ይችላል ያሉት አስተባባሪው÷ በኢትዮጵያውያንና በትውልደ ኢትዮጵያውያን በኩል ቀደም ሲል የተጀመረው የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን የማነጋገር ፣ ስልክ የመደወልና ፊርማ የማሰባሰብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት።
በአሜሪካ ነዋሪ የህወሓት የቀድሞ ተጋይ የነበሩት ወይዘሮ ርስቴ መብርሃቱ÷ የአሸባሪው ቡድን ሀገር የማፈራረስ ተልእኮ ማስፈፀሚያ የሆኑትን ረቂቅ ሕጎች ለመቃወምና እንዳያልፉ ለማድረግ አንድ ሆነን መታገል አለብን፤ እንታገላለንም ብለዋል።
አሜሪካ በታሪኳ ለሰላምና ዴሞክራሲ ብላ እጇን ካስገባችባቸው ሀገራት ትምህርት ወስደን የሀገራችንን ክብርና ነፃነት ለጠላት አሳልፈን መስጠት የለብንም ነው ያሉት ወይዘሮ ርስቴ ፡፡
የውስጥ ችግራችንን በራሳችን መፍታት የምንችልና ለውጭ ጣልቃ ገብነት ፊት የማንሰጥ ህዝቦች መሆናችንን ዳግም ማረጋገጥ አለብን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በትእግስት ስለሺ