Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ቢሆን ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚ ሚና ስትጫወት ቆይታለች – ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ቢሆን ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚ ሚና ስትጫወት ቆይታለች ሲሉ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ገለጹ።

በመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሐም በላይ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክት ለደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት በዛሬው ዕለት አቅርቧል።

ሚኒስትሩ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት አተገባበር ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ በአገሪቱ የተከሰተው ውጥረት ያሳሰበው መሆኑን በመግለጽ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ትግበራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ቢሆን ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚ ሚና ስትጫወት የቆየች አገር መሆኗን በማውሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ወቅት መልዕክተኛ መላካቸውን አድንቀዋል።

ከሰሞኑ በአገሪቱ የታየው ሁኔታ በአግባቡ መያዙን ገልጸው በመተግበር ላይ ያለው ስምምነት ውስብስብ ባህሪያት ያሉት በመሆኑ አልፎ አልፎ መሰል ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሰላም ስምምነቱ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።

ዶክተር አብርሃም በላይ ከተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሪክ ማቻር ጋርም በተመሳሳይ ውይይት አድርገዋል።

በወቅቱ ዶክተር ሪክ ማቻር ኢትዮጵያ አሁን በመተግበር ላይ ያለው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም የመሪነት ሚና መጫወቷን በማስታወስ ይሄንኑ ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ከዚህ ባሻገር ልዑካን ቡድኑ በጁባ ቆይታው ከፕሬዝዳንቱ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ ቱት ጋትሉክ እንዲሁም ከአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር አንጄሊና ቴኒ ጋር ተገናኝቶ መምከሩን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.