Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ ትሥሥራቸውን ማጎልበት አለባቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የምስራቅ አፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትሥሥራቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ተገለጸ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሰልጣን (ኢጋድ) ያዘጋጀው የ’ብሉ ኢኮኖሚ’ ስትራቴጂ በአባል አገራት አስተባባሪ ሚኒስቴሮች ጸድቋል።

የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ÷ የውቅያኖስ፣ የሀይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ብሉ ኢኮኖሚን ከችግሩ ለመውጣት አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሳ ልማት፣ ትራንስፖርት፣ ቱሪዝምና ሌሎች ከውሃ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ምጣኔ ሃብቶችን አገራቱ በትብብር በመጠቀም የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል።

የምጣኔ ሃብት እድገታቸውንና የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በብሉ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች ልምድ መውሰድ እንደሚገባም የካናዳና ሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ጠቅሰዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ÷ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት አገር እንደመሆኗ የብሉ ኢኮኖሚ መዘጋጀቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከአገራዊ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፖሊሲ እንዲሁም ሌሎች እስትራቴጂዎች ጋር በማጣጣም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ ዶክተር ቺሚምባ ዴቪድ ÷ የአፍሪካን በተለይም የምስራቅ አፍሪካን ብሉ ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመጠቀም መንግስታት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአሳ ልማትና አኳካልቸር አስተዳደርን ማጠናከርና በመንግስታት መካከል ትብብርን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን በዘለቂነት ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።

ድርጅታቸው ብሉ ኢኮኖሚ እስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል አገሮች የ’ብሉ ኢኮኖሚ’ ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል።

ለቀጣይ አምስት ዓመታት በኢጋድ አባል አገሮች ተግባራዊ የሚደረገው የ”ብሉ ኢኮኖሚ” እስትራተጂ አካታችና ዘላቂ ብሉ ኢኮኖሚ በማልማት ለቀጣናው የኢኮኖሚ ሽግግር አስተዋጽኦ የማድረግ ራዕይ መሰነቁን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.