“ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፤ለማንም ለምንም አይጠቅምም”-የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፤ለማንም ለምንም አይጠቅምም” ሲል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገለጸ፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፤ ለማንም ለምንም አይጠቅምም ”
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ
ኢትዮጵያ በልጆቿ ውድ መስዋዕትነት የተገነባች ህብረ-ብሔራዊት ሀገር መሆኗ እሙን ነው፡፡ በዘመናት ከውጭና ውስጥ ሲደቀኑባት የነበሩ ፈተናዎችን ድል በመንሳት አንድነቷን ጠብቃ እነሆ ዛሬ ደርሳለች፡፡ ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ በፈተና ውስጥ ሆና በመደመር መንገድ ተጉዛ ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ጋር አንገት ላንገት ተናንቃ ትገኛለች፡፡
ባለፍንባቸው የታሪክ ምዕራፎች የተጋላጭነታችን መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በተሟላ ሁኔታ ዘግተን ባለማለፋችን በጦርነትና በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንቆይ አድርጎናል፡፡በጋራ ታሪክና እሴቶቻችን ላይ የጋራ እይታና መግባባት መፍጠር ተስኖን ግራና ቀኝ ስንጓተት እንስተዋላለን፡፡ህብረ-ብሔራዊነትና ብዝሃነትን የውበታችን ምንጭና መድመቅያችን አድረገን እንደ ጸጋ ከማየትይልቅ እንድ ስጋት ማየታችን ዋጋ ሲያስከፍልን ኖሯል፡፡ባጠቃላይ ሀገራዊ መግባባትን አለመፍጠራችን በየዘመናት የቤት ስራ ሆኖብን እዚህ ደርሷል፡፡
በመሆኑም ባላግባቡን ጉዳዮች ላይ መግባባትን ፈጥረን የችግሮቻችንን ምንጭ ለማድረቅና ሀገረ-መንግስቱን ለማጽናት የተጀመረው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ሀገራዊ ምክክሩ ተሳክቶ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከግጭት አዙሪት ለመላቀቅ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በመደገፍ ላይ እገኛል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ የህብረ-ብሔራዊ አንድነትና የወንድማማችነት ጸር የሆነው ጽንፈኝነት የዜጎች መፈናቀል፤ ሞትና ሰቆቃ መንስኤ በመሆን የሀገራዊ መግባባትና ምክክር ጋሬጣ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከትላንት እስከ ዘሬ በህዝቦች መካካል የኖረው ማህበራዊ መስተጋብር ወንድማማችነት፤ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትና ለሀገራዊ ሉአላዊነትና ክብር አብሮ መቆም ሆኖ ሳለ፤ የህዝባችንን እሴት የማይመጥኑ ጽንፈኞች በሚፈጥሩት መሳሳብ ቀላል የማይባል ሀገረዊ ጉዳትን በማስከትልና እሴቶቻችንን በመሸርሸር ላይ ይገኛሉ፡፡
የነዚህ ጽንፈኞች መሰረታዊ ዓላማ የኦሮሞና የአማራን ህዝብ በማጋጨት ሀገርን ማፍረስ ይቻላል ተብሎ በወያኔ የተወጠነውን ሴራ ማሳካት ነው፡፡ የነኚህን ጽንፈኛ ሀይሎች እኩይ ተግባርን አንድ ቦታ ማስቆም ካልተቻለ በሀገራችን ሌላ አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል፡፡
እዚህም እዝያም የሚታየውን ጽንፈኝነት እያባባሰ ያለው አንዱ ምክንያት በባህሪው ላይ ተመሳሳይ እይታና አቋም አለመያዛችን ነው፡፡በዚሁ መሰረት ጽንፈኝነት ከየትም ይምጣ ከየት እሳቤውና ተግባሩ ጸረ-ህዝብ መሆኑን ተገንዝቦ በጋራ መተጋል ሲገባን ጣት መቀሳሰር ጎልቶ ይታያል፡፡የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ጽንፈኝነት የትም ይብቀል የት ጸረ-ህዝብ መሆኑን በጽኑ አምኖ በመታገል ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሰረት ከአሸባሪው ሸኔ ጋር በሚደርገው ትግል ውድ መሰዋትነት እየከፈለ ይገኛል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚከፈለው መሰዋትነት ጽንፈኝነት ሀገር-አፍራሽ መሆኑን በጽኑ አምነን ሀገርና ህዝብን ለመታደግ እንጂ በአማራ ስም ለሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ሀይሎች እድል ለመከፈት አይደለም፡፡
ከዚህ አንጻር የአማራና የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀንደኛ ጠላት የሆኑት በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ሀይሎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ዘልቀው በመግባት በሰላማዊ ዘጎችና ጸጥታ አካላት ላይ የፈጸሙት አጸያፊ ድርጊት የክልሉን ህዝብ ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ ይህ ጽንፈኛ ሀይል ስለፈጸመው አጸያፊ ድርጊት የክልሉን የመንግስት ሚዲያ ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ሲያስተጋቡ፤ ጥላቻን ሲሰብኩና የግጭት ነጋሪት ሲጎስሙ በዝምታ ማያት ተጋቢ አለመሆኑን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጽኑ ያምናል፡፡
ሕብረ-ብሄራዊነትና ወንድማማችነት ጽኑ የኢትዮጵያ አንድነት መሰረት ነው፡፡መከባበር፤ ለጋራ ሀገራዊ ጥቅም አብሮ መቆም፤ ከልዩነት ይልቅ የጋራ እሴቶቻችንን ማጽናት ዘላቂ መፍትሄ ነው፡፡ ጽንፈኝነት የሚወክለው ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የለውም፡፡ ለማንም ለምንም አይጠቅምም፡፡ ጸረ ህዝብ እሰከ ሆነ ድረስ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ በጋራ ልንታገለው ይገባል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ፊንፊኔ
መጋቢት 26፣ 2014