የሀገር ውስጥ ዜና

የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስፋት የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል- ዶ/ር ይልቃል ከፋለ

By Alemayehu Geremew

April 05, 2022

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ ክልልን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስፋት የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።

ዛሬ ከክልሉ ባለሃብቶች፣ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በኢንቨስትመንት ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ሲሆን በመድረኩ በአማራ ክልል ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት በጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚው በእጅጉ በመጎዳቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውም ተገትቶ ቆይቷል ብለዋል።

በክልሉ ያለውን ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማዘጋጀት ለባለሃብቶች ክፍት ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፥ ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው መዳከም የሃይል ፣ የመሬት አቅርቦት፣ የብድር አገልግሎትና የጥሬ እቃ አቅርቦት አለመኖር ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው አመት ብቻ በክልሉ 780 ፕሮጀክቶች ተገምግመው ቦታ ሳያገኙ የቀሩ ሲሆን፥ 937 ፕሮጀክቶች ደግሞ 880 ሄክታር መሬትን በህገ ወጥ መንገድ አጥረው መገኘታቸውን አመላክተዋል።

በቀጣይ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ የመግባት አቅም ያላቸውን ፕሮጀክቶች በመለየትና ለጥያቄዎቻቸው ፈጣን ምላሽ በመስጠት የክልሉን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግም ገልፀዋል።