በህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የምክክር መድረክ በሀዋሳ ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከዚህ ቀደም በተካሔዱ ህዝባዊ መድረኮች ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያስችላል የተባለ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሄደ፡፡
በምክክር መድረኩ የህግ አውጪ፣ የህግ ተርጓሚና የህግ አስፈጻሚ አካላት በተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች እና መፍትሄዎቻቸው ዙርያ ተወያይተዋል፡፡
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በዚሁ መድረክ÷ የብልጽግና ፓርቲ የጉባኤ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎችን ተከትሎ በክልሉ በ157 ከተሞች ከ66 ሺህ በላይ ህዝብ በውይይት መድረኩ መሳተፉን ተናግረዋል።
በፓርቲው ጉባኤ የተመላከቱ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግም ምን ያህል ከህዝባችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይሔዳል በሚል እና በቀጣይ ስራዎች ላይ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲቻል ሰፊ የህዝብ የምክክር መድረክ ማካሔድ ተችሏል ነው ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ።
በዚህም መሰረት በፓርቲው የተደረሱ ስምምነቶች እና ድምዳሜዎች ይበልጥ በህዝብ ውይይት እንዲዳብሩ መደረጉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በክልሉ ሶስቱ የመንግስት ክንፎች የየራሳቸው ተቋማዊ ነጻነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉም አካላት የህዝብን ፍላጎት በማሟላት ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ ያስችላልም ብለዋል።
በውይይቱም የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ፥ የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥና የግብዓት አቅርቦት ችግር ፤ የፐብሊክ ሰርቪሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ፤የዜጎች ሠላምና ደህንነት አደጋ ላይ መውደቅ ፤የመሰረተ ልማት ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ችግር ፤ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በስብሰባ መጠመድ ፤ በመንግሥት ድጎማ የሚቀርቡ በሌብነት በጥቂቶች ቁጥጥር ስር መውደቅና ህዝቡን ማማረር በሁሉም የስራ መስኮች የደላላ መሳተፍም መንግሥት በቁርጠኝነት መፍታት ያለበት እንደሆነ በሰፊው ከህዝቡ መነሳቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል፡፡
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ ÷ ከህዝብ የሚነሱ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ የፍትህ አሰጣጥ ስርዓትን ማጠናከር ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!