የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጉድለትን በአማራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመተካት እየተሰራ ነው – የክልሎች ግብርና ቢሮ ሃላፊዎች
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በአማራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመተካት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ፣ አማራና ሲዳማ ክልሎች ግብርና ቢሮ ሃላፊዎች ገለጹ።
ለግብርና ግብዓት ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በዋጋ ጭማሪ፣ በመጠንና ጊዜ መስተጓጎል ከወትሮው በተለየ ፈተና ገጥሞታል ተብሏል።
ኦሮሚያ ክልል 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቢያስፈልገውም በግብርና ሚኒስቴር በኩል የሚቀርብለት ድርሻ ግን 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ብቻ እንደሆነ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ጌጡ ገመቹ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው ÷ በምርት ዘመኑ ክልሉ ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ፍላጎት ስላለው እስካሁን 4 ሚሊየን ኩንታል ወደ ክልሉ መድረስ እንደነበረበት እና 1 ሚሊየን ኩንታል ብቻ ተደራሽ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ መስፍን ቀሬ በበኩላቸው ÷ በክልሉ ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አንጻር የጎላ ክፍተት ባይኖርም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ዋጋው ከግማሸ በላይ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ግብዓት የሚያገኙት በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በመሆኑ መንግስት ለማኅበራቱ ዋስትና ይዞላቸው ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ብድር ያመቻቻሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።
ክልሎቹ ያጋጠማቸውን የማዳበሪያ እጥረት ለመፍታት የተፈጥሮ ማዳበሪያን በአማራጭነት ለመጠቀም ማቀዳቸውንም ነው ያስታወቁት፡፡
በኢትዮጵያ በምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 19 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ በመጓጓዝ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!