ቻይና የአውሮፓ ኅብረት አሳሳች መረጃ አነፍናፊ ኤጀንሲዎች ከዩክሬን ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡባትን ውንጀላ ውድቅ አደረገች
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የአውሮፓ ኅብረት አሳሳች መረጃ አነፍናፊ ኤጀንሲዎች በዩክሬን ግጭት ላይ ያለኝን አቋም በተሳሳተ መልኩ አቅርበዋል ስትል ተቃወመች፡፡
የአውሮፓ ኅብረት አሳሳች መረጃ አነፍናፊ ኤጀንሲዎች፥ ቻይና ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ገለልተኛ ነኝ ብትልም በሀገሪቷ መንግስት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ከሩሲያ ጎን ተሰልፈዋል የሚል ውንጀላ አቅርበዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት እና አሜሪካን ያብጠለጥላሉ እና አሳሳች መረጃም ያሰራጫሉ በሚል ወንጅለዋል። ቻይና በበኩሏ ውንጀላውን አጣጥላለች።
ስማቸው ያልተገለጸ አንድ በአውሮፓ ኅብረት የቻይና ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት ÷ ቻይና በዩክሬን በተከሰተው ግጭት ግልጽ እና የማይዋዥቅ ገለልተኛ አቋም አላት፡፡
ሁለቱ ወገኖች በሠላማዊ ንግግር ለግጭቱ እልባት እንዲሰጡ አበክራ ስትጥር ነበር ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
ቻይና ዓለም አቀፉ ህግ ፣ የግጭት አፈታት ባሕል እና የተባበሩት መንግስታት ቻርተር መርሆዎች እንዲከበሩ እና ሁለቱ ወገኖች በትብብር ለዘላቂ ሠላም እና ደኅንነት እንዲሰሩ ትፈልጋለችም ነው ያሉት።