Fana: At a Speed of Life!

ሃይማኖትን የፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌ ሊታረም ይገባል – የሐይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አንዳንድ አካላት የሃይማኖት ተቋማት ከተቋቋሙበት ዓላማ ባፈነገጠ መልኩ ሃይማኖትን የፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ የሚያሳዩት ዝንባሌ ሊታረም እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ በሃይማኖት ተቋማት መካከል በሁለንተናዊ መልኩ መቻቻል ማስፈን ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡
ተቋማቱን የግጭትና የመከፋፈል መሣሪያ የማድረግ ዝንባሌ ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው ያሉት የሃይማኖት አባቶች፥ ይህም ከሃይማኖት መርህም ሆነ ተቋማቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ያፈነገጠ በመሆኑ መቻቻልን ለማስፈን በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ሊታረሙ ይገባል ብለዋል ፡፡
በግንባር ቀደምነት የሃይማኖት ተቋማት በሕዝቦች መካከል መልካም ግንኙነት በመፍጠር እና የምዕመናን ስብዕና በበጎ መልኩ በመገንባት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ በዚሁ ልክ እምነቱን በመቃኘት የአገር ሁለንተናዊ ግንባታን መደገፍ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሃይማኖት ተቋማት መካከል ያሉ የመርሕና የአስተምህሮ ልዩነቶችን በማክበር በመካከላችን መቻቻል ፣ መተሳሰብንና አንድነትን በማጠናከር በሁሉም ረገድ አገሪቱን ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለንም ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማህበራዊ አንቂነትና የፖለቲካ አቋም የሚመስል ነገር በተቋማት ጥላ ስር ሆነው የሚያራምዱ አካላትና ግለሰቦች ጎራቸውን ለይተው ወደ ዝንባሌያቸው መሄድ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ በፓናል ወይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አገራችን በሰላም እጦት በብርቱ እየተፈተነች ያለችበት ወቅት ላይ የምንገኝ በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጋር በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.