Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የ27 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ የመግባቢያ ስመምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ የሚውል የ27 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ሁለቱ ሀገራት ሶስት የመግባቢያ ስምምነቶችን ነው የተፈራረሙት።

ስምምነቱ በ6 ዓመት የሚፈፀም እና በኢትዮጵያ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማጠናከር የሚውል መሆኑ ታውቋል።

በዚህ መሰረት የመጀመሪያው ስምምነት በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ ላይ መሰረት ያደረጉ የስራ ፈጠራ እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ የሚውል ነው ተብሏል።

ስምምነቱ ከተያዘው የፈረንጆቹ 2020 እስከ 2025 ድረስ የሚተገበር ሲሆን፥ ለትግበራው ማስፈጸሚያም 10 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት መያዙን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሁለተኛው ስምምነት ደግሞ በ8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚከናወን እና በአጠቃላይ ለ6 ዓመታት የሚተገበር መሆኑም ታውቋል።

ስምምነቱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት አመራሮች እና ሰልጣኞችን አቅም ግንባታ ለማሳደግ ይውላልም ነው የተባለው።

ሶስተኛው ስምምነት ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአፋር ክልሎች የጨቅላ ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ መሆኑም ነው የተነገረው።

በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ድጋፉ ለ5 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፥ በአጠቃላይ የ9 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት እንደተያዘለትም ነው የተገለፀው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.