Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት በሸቀጦች አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የጋረጠው ፈተና ለአፍሪካ የማንቂያ ደወል ነው – ዶ/ር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት በሸቀጦች አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የጋረጠው ፈተና ለአፍሪካ የማንቂያ ደወል ነው ሲሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ አስታወቁ፡፡

የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዛሬ ባዘጋጀው የበይነ መረብ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ስብሰባው ‘‘የአፍሪካ ነጻ ገበያ ቀጠና ይዞ የመጣውን ጥቅም የትራንስፖርት ወጪን በመቀነስ ማሳደግ’’ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነው፡፡

ዶክተር ፍጹም በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና በትክክለኛው መንገድ ከተተገበረ በአህጉሪቱ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ የመለወጥ አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ከቀጣናዊ ንግድ ጋር በተገናኘ በቅርብ ጊዜያት ለውጥ አለ ያሉት ሚኒስትሯ ፥ ከሌሎች ዓለማት ጋር ሲነጻጸር ግን አፍሪካ ወደ ኋላ መቅረቷን በማመልከት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ትግበራ ስኬታማነት ይህን ክፍተት የሚሞላ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና በመላው አህጉሪቱ ኢኮኖሚውን በማሳደግ፣ የንግድ እና ሥራ ፈጠራን በማሻሻል ለሸቀጦች እና አገልግሎቶች አንድ የንግድ ማዕከል በመገንባት ድህነትን በመቀነስ ረገድ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡

ሆኖም አገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን በመቀላቀል ከትሩፋቱ እንዳይቋደሱ እንቅፋት መሆኑንና ይህም የሆነበት በትራንስፖርት መሠረተ ልማት እና በሎጂስቲክስ አለመሟላት ምክንያት መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡

የታሪፍ ቅናሽን ጨምሮ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚገኙ ትሩፋቶችን በሚገባ ለመጠቀም ይኸው ደካማ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ያላቸው አገራት ማሻሻያ ማካሄድ፣ ለግጭቶች መፍትሔ ማበጀት፣ ሙስናን መዋጋት እና የጉምሩክ አሰራራቸውን ማሻሻል እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም የመሠረተ ልማቶችን ከማሻሻል እኩል ዘመናዊ አሰራሮችን መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነም ዶክተር ፍጹም በስብሰባው ላይ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ስብሰባ ከሦስት ዓመት በላይ የዘለቀው የኮሮና ቫይረስ እና በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ የሚገኘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በሸቀጦች እና አገልግሎቶች አቅርቦት ሰንሰለት ፈተና መጋረጡን አስታውሰው ፥ እነዚህ ክስተቶች ለአህጉራችን አፍሪካ የማንቂያ ደወል መሆናቸውንና የአፍሪካንም አቅም ማጋለጡን አመልክተዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ አፍሪካ በአህጉሩ የዳበረ እና የተሳለጠ ንግድ እንዲኖር በማድረግ ከአፍሪካ ውጭ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ እንደምትችል ያመለከቱት ዶክተር ፍጹም ፥ ሆኖም ግን ይህ እውን እንዲሆን አገራት ምርታቸውን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተናበው ማስኬድ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ከአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዋነኛ ፕሮጀክቶች መካከል ሲሆን ፥ በንግድ እና ኢኮኖሚ ትስስር ሁሉን አካታች እና ዘላቂ እድገትን ለማምጣት የሚሠራ ነው፡፡

ከኤርትራ በስተቀር ሁሉም አገራት የፈረሙት የዚህ ፕሮጀክት ስምምነት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ42 አገራት የጸደቀመሆኑ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.