Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
 
አምባሳደር ዲና ዛሬ በጎንደር ከተማ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም መንግስት ለእርዳታ እና ሰላም ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው ሳምንት 20 ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ የገቡ መሆኑን አስታውሰው፥ መንግስትም ይህን ድጋፍ ለማስቀጠል ዝግጁነቱ እንዳለው ቃል አቀባዩ አመላክተዋል።
 
ነገር ግን ህወሓት በእርዳታ አቅርቦት ሂደቱ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
 
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና እድልን ለማስፋት መሰራቱን ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ በእስራኤል የቱሪዝም አውደ ርዕይ መካሄዱን ተናግረዋል።
 
በህንድ የአፍሪካ ንግድ ፎረም መካሄዱን በመጠቆም በአንካራ እና ሱዳን መሰል የኢኮኖሚ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል።
 
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የዓባይ የህብረ ዝማሬ ምርቃት እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማእከል መመስረቱን በመግለጫቸው አንስተዋል።
 
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለመደበኛው ዲፕሎማሲ ስራ አጋዥ መሆኑን እና በአሁኑ ሰዓት በተለይም፥ የውጭ ተጽዕኖን ከመቋቋም አንጻር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
በትናንትናው እለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአሜሪካ እና አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ሁኔታ ላይ መወያየታቸውንም ጠቁመዋል።
 
የጂቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ዑመር ጌሌ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት እና የነበሩ ሁነቶችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አምባሳደሮችም ኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ እንዳይፀድቅ የዲፕሎማሲ ስራ መስራታቸውን አስረድተዋል።
 
በመግለጫቸው ኤርትራ በኢትዮጵያ ከአምባሳደር ደረጃ ወደ ጉዳይ አስፈጻሚ ማውረዷን በተመለከተም ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ ይህ መሆኑ የሃገራቱ ግንኙነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም ብለዋል። ሀገራቱ ያላቸው ግንኙነትም ጤናማ መሆኑን አረጋግጠዋል።
 
በለይኩን አለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.