Fana: At a Speed of Life!

ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ለገቡ ዜጎች አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30 ፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ለገቡ ዜጎች አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ እየተደረገ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ለገቡ እና ለሚገቡ ዜጎች አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ እየተደረገ ነው።

በዚህ መሠረትም በሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ ጃራ በሚባል ቦታ 88 ሺህ በላይ ዜጎችን መያዝ የሚችል 400 ሄክታር መሬት ላይ መጠለያ በመስራት አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ እና ቁሳቁስ የማሟላት ስራ አየተከናወነ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በደቡብ ወሎ ዞን ሃይቅ ከተማ አካባቢ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች የሚጠለሉበት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ አገልግሎት እየሠጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ እና የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችንም ወደ ማዕከሎቹ የማጓጓዙ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

በዋግኸምራ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮችን በሰቆጣ ከተማ አካባቢ መጠለያ ካምፕ ተዘጋጅቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ በዚህም አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶ ተፈናቃዮች መግባታቸውን ተናግረዋል።

ተፈናቃዮችን በመጠለያ ጣቢያዎች የማስፈሩ ስራም ለመረጃ እና አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው ያስረዱት።

በቀጣይ በመጠለያ ጣቢያዎቹ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት አዲስ የሚመጡ እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የትግራይ ተፈናቃዮችን ወደ ተዘጋጁት መጠለያዎች የማስገባቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ምግብ እና ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን ለማዳረስ በመንግስት የሚደረገው ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑም አጋር አካላት እና የተራድኦ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በሌላ በኩል አሸባሪው ህወሓት በሚፈጽመው ትንኮሳ እና ወረራ ከአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዋግኸምራ ብሔረሰብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ እየተሠራ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የሽብር ቡድኑ በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሚፈጽመው ትንኮሳ እና ወረራ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ዋግኸምራ ሰቆጣ ከተማ እና ሰሜን ወሎ ዞን ከተሞች የሚመጡ ዜጎች ቁጥር ከቀን ቀን እየጨመረ ነው።

አሁን ላይ በሁለቱ ዞኖች የሚገኙ አዲስ ተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከ124 ሺህ 200 በላይ መድረሱን ነው የገለጹት።

ተፈናቃዮቹ በመጠለያ ጣቢያዎች እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ተጠግተው እንደሚኖሩ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ፥ ለዜጎቹ አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመላኩ ገድፍ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.