Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ ከተሞች ወጣቶች ”የፈተናዎች መብዛት ከብልጽግና ጉዟችን አያስቆመንም” በሚል መሪ ሃሳብ መከሩ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ”የፈተናዎች መብዛት ከብልጽግና ጉዟችን አያስቆመንም”በሚል መሪ ሃሳብ የወጣቶች የውይይት መድረክ በተለያዩ ከተሞች ተካሄደ።
በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘነው የምክክር መድረኩ የጋምቤላ ክልል ወጣቶች እና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ከክልሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሯች ባየክ ወጣቱ ትውልድ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ግንባር ቀደም ሆኖ ሊንቀሳቀስ ይገባል ያሉ ሲሆን ፥ የብልጽግና ፓርቲ ፈተናዎችን እየተሻገረ እዚህ መድረሱን አንስተዋል፡፡
በቀጣይም መልካም ጎኖችን እያጠናከሩ ድክመቶችን እያረሙ የሚደረገው ጉዞ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ መልካም ጅምሮች እና ፈተናዎች ላይ ለመወያያነት በቀረበው ጽሁፍ፥ ያለፉት ዘመናት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፈተናዎች፣ ብልጽግና ፈተናዎችን ለመፍታት ያደረጋቸው ጥረቶች እንዲሁም ሀገር በቀጣይ ወደ ተሻለ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መግባት በምትችልባቸው አቅጣጫዎች ላይ የውይይት ሃሳብ ቀርቧል።
የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሪት አባንግ ኩመዳን በበኩላቸው ፥ ወጣቱ ክፍል የልማት አቅም እና ሃይል በመሆን የነገውን የክልላችን እና ብሎም የሀገራችን ተረካቢ ለመሆን ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የክልሉ ካቢኔ አባላት፣ የጋምቤላ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አደረጃጀት አመራርና አባላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታርያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ‘‘ውሳኔዎችን ተግባራዊ በማድረግ የወጣቶች ሚና’’ በሚል ርዕስ የሐረሪ ክልል ወጣቶች ውይይት አድርገዋል።
የፈተናዎች መብዛት ከብልፅግና ጉዟችን አያስቆመንም በሚል ወጣቶቹ የብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ ውሳኔዎች ለተግባራዊነታቸው የወጣቶች ሚና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
በውይይት መድረኩ ላይ የሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲያችና የሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሐሰን አብዲ እንደተናገሩት፥ የብልፅግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ ለወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ወሳኝ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን አስታውቀዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ስራ አስፈፃሚ አባል ወጣት መለሰ አባተ ፥ ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው የሀገርን ብልፅግና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ወሳኔዎችን ማስተላለፉን ገልጸዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችንና ሃሳቦችን ያቀርቡ ሲሆን ፥ በዚህም ለአሁኑ ሃገራዊ ለውጥ የወጣቱ ሚናና አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደነበርና ወጣቱ አሁን ላይ በስራ አጥነት ችግርና የስራ እድል ውስንነት እየተቸገረ መሆኑን ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ የመልካም አሰተዳደር ችግር እንደሚስተዋል፣ ወጣቱ ለማጠይቃቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ያለመስጠትና ሊካሄድ በታሰበው ሃገራዊ ህዝባዊ የምክክር መድረክ ላይ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ሁኔታዎች መመቻቸት እንደሚኖርባቸውና መንግስትም የወጣቱን ችግር ወርዶ በማየት ለመፍትሔው መጣር እንደሚኖርበት አንስተዋል።
ከወጣቶቹ የተነሱን ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አባላት ምላሽ ተሰጥቶበታል።
በተመሳሳይ የብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው ባሳለፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገው የወጣቶች የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን ፥ ከ800 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሶማሌ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ አሚና ኢብራሒም እንዳሉት ፥ ያለፈው ትውልድ ሀገር ለመፍጠር እና ለመገንባት የከፈሉት ዋጋ እነርሱ የወቅቱን የትውልድ አደራ መወጣታቸውን የሚያሳይ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ወጣቶች ሊግ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወጣት መርዎ አደም ፥ የወጣቱ ጥያቄ ቀዳሚ ስፍራን የሚይዝ መሆኑን በመገንዘብ ወጣቶች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ በአደረጃጀታችን ትግል እናካሂዳለን ስትል ገልጻለች፡፡
መድረኩን የመሩት በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የወጣቶች ሊግ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የሊጉ ስራ አስፈጻሚ አባል ወጣት ይልማ ተረፈ ፥ በጉባኤው ውሳኔዎች ላይ ተመርኩዘው ወጣቶች ለጥቅምና መብቶቻቸው መከበር በጥልቀት ሐሳብ የሚያቀርቡበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን÷ ለብልጽግና ፓርቲ ውሳኔዎች መሳካት የሚጠበቁ ተልዕኮዎች ላይ ሁሉም መረባረብ እንደሚገባው የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ሙሴ አስገንዝበዋል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

ተጨማሪ መረጃ ፡ – ከክልሎቹ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.