Fana: At a Speed of Life!

ለጋሽ አገራት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ሰብዓዊ ድጋፍ በዕጥፍ መጨመር አለባቸው- ድርጅቱ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ለጋሽ አገራት የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ በዕጥፍ እንዲያሳድጉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ጥሪ አቀረበ።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት እና በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በርካታ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ሜተክ ማጅ ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱና በድርቁ ተጎጂ የሆኑ ከ11 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን እና ከ700 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች አሁን ላይ የለጋሾችን አስቸኳይ ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለእነዚህ ተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ሲሉም ተናግረዋል።

እስከ ፈረንጅቹ 2022 ዓመት መጨረሻ ድረስ የሰብአዊ እርዳታ የሚፈልጉ ተጎጂዎች ቁጥር በትንሹ 20 ሚሊየን እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል።

ለተጎጂዎቹ የሚያስፈልገው ሰብዓዊ እርዳታ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን ጠቅሰው÷  ለጋሽ አገራት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ሰብዓዊ እርዳታ በዕጥፍ እንዲጨምሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የተረጂዎች ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሶማሌ ክልል ለእያንዳንዱ ተረጂ ሲሰጥ የነበረውን የ15 ኪሎ ግራም ወርሃዊ የጥራጥሬ ድጋፍ ወደ 12 ኪሎ ግራም መቀነሱን ጠቅሰዋል።

ላለፉት 3 ተከታታይ ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጠው የምግብ ድጎማ ከ18 በመቶ ወደ 16 በመቶ መቀነሱንም አክለዋል።

ድርጅቱ በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ለ3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ባጋጠመው ድርቅ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች ተጎጂ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ለ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ተጎጂዎች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ከግጭት ማቆም ውሳኔ በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 20 ተሽከርካሪዎችና አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም 35 ተሽከርካሪዎች የአፋር ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በጦርነቱ በተጎዱ የአማራና አፋር ክልል የተለያዩ  ዞኖች ውስጥ ባደረገው የምግብ ዋስትና ዳሰሳ÷ በአካባቢው ከሚኖሩት 98 በመቶ ያህሉ ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር መዳረጋቸውን አረጋግጧል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.