የሀገር ውስጥ ዜና

በደብረ ብርሃን በደረሰው የእሳት አደጋ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ በሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

By Alemayehu Geremew

April 11, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረ ብርሃን ከተማ ትናንት ሌሊት በደረሰ የእሳት አደጋ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ በሚገመት የግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማው ፖሊስ ገለጸ።

የእሳት አደጋው የደረሰው በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት እና በአንድ ዳቦ ቤት ላይ መሆኑን የሦስተኛ ፓሊስ ጣቢያ ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ዳግም አጣለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የአደጋው መንስኤ ከኤሌክትሪክ አጠቃቀም ስህተት ጋር የተያያዘ መሆኑን ኮማንደር ዳግም አመላክተዋል።

ትናንት ከሊሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ በደረሰው በዚሁ አደጋ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት አንድ ተሽከርካሪ ላይ ጉዳት ሲደርስ ግምቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን እንዲሁም ጀኔሬተር መውደሙ ተገልጿል፡፡

በአደጋው 13 በጎችም እንደተቃጠሉ እና በአጠቃላይ ግምቱ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት መውደሙን የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።

የእሳት አደጋው በአካባቢው ተሥፋፍቶ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በህብረተሰቡ ርብርብና በእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ተመልክቷል።

በሰላማዊት ሙሉነህ