በአነስተኛ ኢንዱስትሪ የምግብ ዘይት ሲያመርቱ የቆዩ ተቋማት ከገበያ እንዳይወጡ ባለድርሻ አካላት ሊተባበሩ እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአነስተኛ ኢንዱስትሪ የምግብ ዘይት ሲያመርቱ የቆዩ ተቋማት ከገበያ እንዳይወጡ ባለድርሻ አካላት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለፀ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ÷ በአነስተኛ ኢንዱስትሪ ዘይትን አምርተው ለተጠቃሚዎች ሲያቀርቡ የቆዩ ተቋማት የፋይናንስና ቴክኒካል ድጋፍ በሚፈለገው ደረጃ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል ።
የፋይናንስ ተቋማት የተጓተቱ የቢሮክራሲ አሰራሮችን ቀልጣፋ በማድረግ ሊያግዟቸው ይገባል ያሉት አቶ ጳውሎስ በርጋ ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የቅባት እህሎች ለዘይት አምራቾች በስፋት የሚቀርቡበት መንገድ ሊመቻች እንደሚገባም አብራርተዋል ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትም ጉዳዩ በፖሊሲ ዙሪያ እንዲታይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የዘይት አምራች አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም የድጋፍ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል ።
መንግስትም ለዘርፉ በቂ ትኩረት ቢሰጠው የሃገር ውስጥ ፍጆታን ለመሸፈን ጥረት ማድረግ ይቻላል ብለዋል ።
ከፍተኛ የስራ እድልን መፍጠር እና የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት እንደሚቻልም ባለሃብቶቹ አመላክተዋል።
በአወል አበራ