የኢትዮጵያ አጠቃላይ የጤና ወጪ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አጠቃላይ የኢትዮጵያ የጤና ወጪ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ይህን የገለጸው የሥምንተኛውን ዙር የኢትዮጵያ የጤና ወጪ ጥናት ውጤት በአዲስ አበባ ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።
በ2009 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የጤና ወጪ 72 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት ተከታታይ እድገት በማሳየት ወደ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ደርሷል ነው የተባለው።
በሥምንተኛው ዙር የጤና ወጪ ጥናት ውጤት መሠረት የሀገሪቱ የጤና ወጪ በነፍስ ወከፍ ደረጃ ከነበረበት 33 ነጥብ 21 የአሜሪካ ዶላር ወደ 36 ነጥብ 30 የአሜሪካ ዶላር ማደጉ ነው የተመለከተው፡፡
ይህ የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ በዓለም የጤና ድርጅት ከተቀመጠው አንጻር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው ተብሏል።
በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ካሉ ሀገራት አንጻር ሲታይም በ43 የአሜሪካ ዶላር ዝቅ ይላል።
በታሪኩ ለገሰ