ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ህጎች ከመፅደቅ መዘግየት የሚፈጥረውን መልካም እድል መጠቀም ይገባል – የኢትዮ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ህጎች እንዲዘገዩ መደረጋቸው የበለጠ ተረባርቦ ውድቅ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ጊዜ የሚሰጥ ቢሆንም የመንግስትን እጅ ለመጠምዘዝ የሚያስችል እድል ሊፈጥር እንደሚችል የኢትዮ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ይገልጻል።
የምክር ቤቱ ሊቀመንበር ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ረቂቅ ህጎቹን በገንዘብ የደገፉ አካላት የመዘግየቱን አጋጣሚ ተጠቅመው ድጋፍ በማሰባሰብ እየተጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይም ረቂቅ ህግቹ በአጣዳፊ ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ተብለው ከተቀመጡበት የ8ኛ ደረጃ ወደ 336ኛ ተራ ተደብቀው ቅደም ተከተል እንዲታዩ ተወስኖባቸዋል ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የሚፈልጉትን እንዲያደርግ እንደማስፈራሪያ ሊጠቀሙበት ማሰባቸውን ያመላክታል ብለዋል ሊቀመንበሩ።
በምክር ቤቱ የማህበራዊ ሚዲያ ዳይሬክተርና የዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ሀብተወልድ በበኩላቸው፥ ረቂቅ ህጉ እንዲዘገይ መደረጉ ሊያዘናጋ አይገባም ባይ ናቸው።
በኢትዮጵያውያን ጥረት የተገኘ ስኬት ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረግ አልያም እስከ መጪው ምርጫ ድረስ ሳይጸድቁ እንዲቆዩ ማድረግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ምክር ቤቱ ረቂቅ ህጎችን ውድቅ ለማድረግ ከቀድሞው በበለጠ ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም ነው የስራ ሃላፊዎቹ የተናገሩት።
በተሳሳተ ግንዛቤ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በጥምረት እየሰሩ የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም ሀገርን ለማዳን ቅድሚያ ሰጥተው ረቂቆቹን መታገል እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በትእግስት ስለሺ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!