የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚውል የ300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ለተዘጋጀ ፕሮጀክት የሚውል የ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አፀደቀ።
ባንኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ይህ ዓለም አቀፍ የልማት ድጋፍ በኢትዮጵያ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እንደሚውል አስታውቋል።
በተለይም ድጋፉ የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦትን ለማሻሸል እና ለዓየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መሰረተ ልማት ለመገንባት እንደሚውል በመጠቆም፥ በግጭት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚያስቀድም ነው ባንኩ ያመለከተው።
በዚህም መሰረት አፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አስታውቋል።
በአጠቃላይ ድጋፉ ከ5 ሚሊየን የሚበልጡ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው ባንኩ በመግለጫው ያስታወቀው።
ውጤታማ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም በማሰብ የገንዘብ ድጋፉ በፌደራል መንግስት፣ በክልል መንግስታት እና በአካባቢዎቹ በሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኩል እንደሚቀርብም ገልጿል።