የግሉ ዘርፍ ያልመራው የክህሎት ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ይሳካል ተብሎ አይታሰብም – አቶ ንጉሡ ጥላሁን
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የግሉ ዘርፍ ያልመራው የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የኢንዱስትሪ ሰላም ማረጋገጥ እንደማይቻል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተናገሩ፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ጋር በመተባበር የአሠሪና ሠራተኛ ተወካዮች፣ ኢንዱስትሪዎች እና ባለድርሻ እና አጋር አካላት በተገኙበት በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ ተወያይቷል፡፡
አቶ ንጉሡ ጥላሁን በመድረኩ ላይ እንደገለፁት÷ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ገበያ ፍላጎትና የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት አለመጣጣም ይስተዋላል፡፡
ይህም የማክሮ ኢኮኖሚው ትልቁ ችግር የሆነውን የሥራ አጥነት ቁጥር ከፍ እንዲል ያደረገ ሲሆን÷ መንግስት ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ስትራቴጂያዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ አምኖ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የክህሎት ልማቱ የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ እንዲሆን፣ የሥራ አጥነት ችግሩን ለመፍታት፣ የአሠሪና ሠራተኛው ግንኙነት እንዲሰምር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሰላምን አጣጥሞ ለመምራት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሰነዱ ተቋማዊ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና የዜጎችን ተስፋ ለማለምለም አስተዋጽኦው ከፍተኛ በመሆኑ ተሳታፊዎች በቆይታቸው በኃላፊነት መንፈስ እና በታላቅ ጥንቃቄ ሰነዱን እንዲያዳብሩ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ተወካይ አይዳ አወል በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የቴክኒክና ሙያ ተደራሽነትን ለማስፋት ባደረገችው ጥረት ተጨባጭ ውጤቶች እንዳስመዘገበች ገልጸው ዘርፉ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት አንስተዋል፡፡
የክህሎት ልማት ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት፣ ድህነትን ለመቀነስ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሥራ ገበያው በሚፈልገው ሙያና ክህሎት ወጣቶችን ማብቃት እንዳለባት ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ የሚሰበሰበው ግብዓትም በቀጣይ ለሚዘጋጀው የቴክኒክና ሙያ ፖሊሲ ጥራት ወሳኝ መሆኑ መመላከቱን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡