Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር በፍጥነት እንድትወጣ የዳያስፖራው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር በፍጥነት እንድትወጣ የዳያስፖራው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይባል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አአምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው÷ መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ላደረጉ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም የሰብአዊ መብት ድጋፍ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይቀመጥለት ተጠናክሮ ሊካሄድ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ለኦሊሴጉን ኦባሳንጆን ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መምጣታቸውንና በሰላም ጥረቶች፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ለአንድ ወገን ያደላ እና አስፈላጊ መርሆዎችን የማያሟላ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና÷ መንግስት ግን ተፈጽመዋል የተባሉ ጥፋቶችን ለማጣራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በካናዳ እና በአሜሪካ ከሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ተወካዮች ጋር ምክክር መደረጉን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት ውስብስብ ችግሮች ትወጣ ዘንድ የዳያስፖራው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከደቡብ ኮሪያ አቻቸው ጋር በተወያዩበት ወቅት ኢትዮጵያ ደቡብ ኮርያ በችግር ላይ በነበረችበት ጊዜ የደረሰችላት አገር በመሆኗ ውለታዋን እንደማትዘነጋ አውስተው፥ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራም ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ ሰላምንና መረጋጋትን ለማስፈን እየሰራች እንደምትገኝም አምባሳደር ሬድዋን ማስረዳታቸውን አንስተዋል።
የእስራኤል የሀኪሞች እና የፓርላማ አባላት የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ እንደሚገኙና በጦርነት የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በማገዝ ላይ እንደሚገኙም አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በሳዑዲ አረቢያ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ በቀን ሶስት በረራዎች እየተደረጉ መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሰነዶችን የሚቃወሙ ሰልፎች በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች እና በቤልጅየም ብራሰልስ መካሄዳቸውን እና በሌሎች የአለም ክፍሎችም በቀጣይ እንደሚካሄዱ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ወደ ትግራይ ያልተገደበ ድጋፍ እንዲደርስ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው÷ ነገር ግን ህውሓት በኃይል ከያዛቸው አካባቢዎች መውጣት እንደሚኖርበት ለአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ገለጻ መደረጉን አንስተዋል፡፡
ኤርትራ በኢትዮጵያ የመደበቻቸው ጉዳይ አስፈጻሚ የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያውቁና ግንኙነቱን የበለጠ ማጠናከር የሚችሉ ግለሰብ መሆናቸውንም ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደረጋቸውን በወልቃይት በህወሓት የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን የሚያመላክቱ ጥናታዊ መረጃዎች ገለልተኛ አካላት እንዲያረጋግጡት መጋበዙንም አንስተዋል፡፡
የአሰራር መርሆዎችን የሚጥሱ የረድኤት ድርጅቶችን መንግስት እንደማይታገስም ነው አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ያነሱት፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.