Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ 485 የአሜሪካ እና የካናዳ ምክር ቤት አባላት ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አገደች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ 485 የአሜሪካ እና የካናዳ ምክር ቤት አባላት ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ ማገዷን አስታወቀች።

ሩሲያ በሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት ላይ ውሳኔውን ያስተላለፈችው በዚህ ዓመት መጋቢት 24 ቀን አሜሪካ በ328 የሩሲያ ምክር ቤት (ዱማ) አባላት ላይ ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

ሩሲያ ወደ አገሯ እንዳይገቡ ማዕቀብ የጣለችው በ398 የአሜሪካ፥ በ87 የካናዳ የምክር ቤት እና የሴኔት አባላት ላይ ነው።

በተመሳሳይ ቀን የነጩ ቤተ-መንግስት ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ኃላፊ የሆኑት ጄን ሳኪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ አሜሪካ በቀጣይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ካላቆመች ተጨማሪ ማዕቀቦች ልትጥል እንደምትችል አስጠንቅቃለች፡፡

አሜሪካ ተጨማሪ የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ብታስጠነቅቅም የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን፥ “ማንም (የውጭ ኃይል) የሩሲያን በሮች እና መስኮቶች ሊዘጋ አይችልም፤ አሁን ያለፈው የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አክትሟል፤ ማንም ሩሲያ ላይ የበላይነቱን ማሳየት አይችልም” ብለዋል፡፡

ቭላድሜር ፑቲን ይህን የገለጹት ከቤላሩሱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

ሁለቱ ሀገራት ምዕራባውያኑን ለመጋፈጥ ትሥሥራቸውን እና ወዳጅነታቸውን ማጠናከራቸውንም ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.