“ሰላም መቶ በመቶ ያሸልማል” መርሃ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊነት አስመልክቶ “ሰላም መቶ በመቶ ያሸልማል” በሚል መርህ የተዘጋጀው መርሃ ግብር በሚሊኒየም አደራሽ በድምቀት ተካሄደ።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌደሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሸን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የመግስት ስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀዳ ስንቄዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ታድመዋል።
በመርሃ ግበሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሽልማቱ በኢትዮጵያ ለሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦች ከዚህ በኋላ በየዓመቱ የሚሸለመቱን ሽልማት እና የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆናቸው ከሀገሪቱ የሰላም ቤተሰቦች የተበረከተላቸውን ሽልማት ነው።
በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኖቤል ሽልማቱ እንደ ሀገር እንድንኮራ ብሎም ለበለጠ እውቅና እንድንዘጋጅ የሚጋብዘን ነው ብለዋል።
ዓለም ሀገራችንን ከሰላም ጋር ያስተሳረበት እና ተስፋ የታለባትም ክስተት መሆኑን ነው ያነሱት።
ለሰላማዊ መፍትሄ ሁልጊዜ ቀዳዳ እንዳለ የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፥ውይይታችን ከግለሰብና ከቡድን ፍላጎት ባለፈ ብቸኛ ሀገራችን ላይ ያተኮረ መሆን አለበት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው በመልዕክታቸው የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን፣ እንታቸውን እና ባለቤታቸውን አመስግነዋል።
ሁላችንም በውስጣችን ሰላም ሊኖረን ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በውስጥ ሰላም ከሌለ ወደ ውጭ የሚወጣ ሰላም የለም ብለዋል በመልዕክታቸው።
መላው ኢትዮጵያውን ታዳጊዎችም በችግር ውስጥ ቢሆኑም ትልቅ ዕያለሙ በሌሎች ዘርፎች ስሟ እንዲጠራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው ሽልማቱ ለአፍሪካዊ የግጭት አፈታት ሂደት እውቅና የሰጠ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሽልማቱ የሁሉም ኢትዮጵያው ነው ያሉት ደግሞ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው።
ወይዘሮ ሙፈሪያት ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ እንድትደርስ ኢትዮጵያውያን ሰውነትን አስቀድመን እንዋደድ ብለዋል፤ ይህን ማድረግ ከቻልን ሀገሪቱ ከልጆቿ አልፋ ከዓለም ሁሉ ለሚመጡ የተትረፈረፈ ሀብት አላት ነው ያሉት።
ሀገር መለወጫ እና መተኪያ እንደሌላት ያነሱት ሚኒስትሯ ሁላችንም በጋራ ከተነሳን፤ ጥላቻን እና መናናቅን ካስወገድን ይህንን መስቀለኛ መንገድ መሻገር እንችላለንም ብለዋል።