የሀገር ውስጥ ዜና

ግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በስፋት ለመጠቀም በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ገለጸ

By Alemayehu Geremew

April 15, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩትን የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና “ቨርሚ” የተሰኘ ኮምፖስት በስፋት ለመጠቀም ሥራዎች መጀመራቸውን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስቴር የአፈር ልማት ማሻሻያ ዳይሬክተር ተፈራ ሰሎሞን እንደገለፁት ÷ ምንም እንኳን የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያን ሙሉ በሙሉ መተካት ባይችሉም ሁለቱን የማዳበሪያ ዓይነቶች እንደሁኔታው በማጣመር መጠቀም ግን የተከሰተውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አሁን የገጠመውን እጥረት ከመሸፈን በተጨማሪ በማዳበሪያ እጦት ሳቢያ የምርት እጥረት እናዳያጋጥም ድርሻው የላቀ መሆኑን አቶ ተፈራ ተናግረዋል።

በቀጣይ ዓመት የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት ለማዳረስ የግብርና ሚኒስቴር በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሮች ÷ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥሩ አማራጭ ቢሆንም በስፋት አልተሰራበትም ብለዋል።

በአልማዝ መኮንን