Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ከፍተኛ ጥረት አደንቃለሁ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደንቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ በመስኖ የለማ ስንዴን ዛሬ ጎብኝተዋል።
 
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጎበኘው በወረዳው አባይ ቀበሌ በ167 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ማሳ ነው።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት በአማራ ክልል የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ከፍተኛ ጥረት አደንቃለሁ ብለዋል።
 
“በክላስተር የግብርና አካሄዳችን በአንድነት ለምግብ ዋስትና እና ለሀገር ልማት ምን እንደምናሳካ ማሳያ ነው” ብለዋል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ።
 
አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከዚህ በፊት ስንዴን በመስኖ የማልማት ልምድ እንዳልነበራቸውና በዚህ አመት ግን የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ እንዳደረጉ ተናግረዋል።
 
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በዘመናዊ ማሽን እርሻ በማረስ፥ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በማቅረብ እገዛ እንዳደረገላቸው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።
 
በበጋ የሚለማ ስንዴ በሽታና ብርድ የማያጠቃው በመሆኑ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁና አሁን ሰብሉ ያለበት ቁመናም በሄክታር እስከ 40 ኩንታል እንደሚያገኙበት ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
 
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በዞኑ ከሚለማው መሬት ከ90 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
 
በአላዩ ገረመው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.