የሀገር ውስጥ ዜና

የሲዳማ ክልል የፊቼ ጨምበላላ በዓልን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን አስታወቀ

By Feven Bishaw

April 15, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል ከሁለት ሳምንታት በኃላ እንደሚከበር የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ለበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሀላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ÷በዓሉን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት በዓሉ በቤት ውስጥ መከበሩን አስታውሰዋል፡፡

ዘንድሮ ግን በዓሉ በአደባባይ ባህላዊና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚከበር ጠቅሰው፥ አሁንም በዓሉ ሲከበር ግን የኮቪድ -19 ወረርሽኝ መከላከያ ፕሮቶኮል መመሪያዎችን በጠበቀ መልኩ ነው ብለዋል፡፡

የበዓሉን ቀን የሚወስኑት የሲዳማ አያንቱዎች መሆናቸውን ያነሱት ሃላፊው አያንቱዎች በባህሉ መሠረት ዘጠኝ ቀን ሲቀረው የበዓሉን ቀን ይፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የፊቼ ጨምበላላ በዓል ከሰባት ዓመት በፊት በተመድ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በመመዝገቡ ዓለም አቀፍ በዓል ሆኖ የሚከበር ነው ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ለጨምበላላ በዓል ወደ ሀዋሳ ከተማ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ጥሪ ማድረጉን ጠቅሰው፥ በፊቼ ጨምበላላ በዓል ላይም የክልሉን የቱሪዝምና ሌሎች እምቅ ሀብቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

ከፊቼ ጨምበላላ ዕሴቶች ውስጥ ለተፈጥሮና ለፈጣሪ ክብር መስጠት ዋነኛ መሆኑና ያለው ለሌለው ማካፈል ዕሴቱንም አክባሪዎቹ እንዲተገብሩት ጥሪ ቀርቧል፡፡

በተመስገን ቡልቡሎ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ! ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!