Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሚካሄደውን የሰላም ጥረት ይደግፋል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሚካሄደውን የሰላም ጥረት እንደምትደግፍ አረጋገጡ።

አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም አቶ ደመቀ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በመውሰድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በእስር ላይ የነበሩ ታዋቂ ፖለቲከኞች መፈታታቸውን፣ በመላ አገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱን እና ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን አንስተዋል፡፡

መንግሥት በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ እንዲዳረስ ለማድረግ የተናጠል የግጭት ማቆም ማድረጉን አብራርተዋል።

ለአብነትም ወደ መቐለ ከሚደረጉ ተከታታይነት ካላቸው የእርዳታ ጫኝ አውሮፕላን በረራዎች በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በሚንቀሳቀሰው የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስተባባሪነት የትናንቱን ጨምሮ እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ጋር ወደ መቐለ እየተጓዙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህ ወቅትም አቶ ደመቀ መኮንን መንግስት በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አማካኝነት የሚካሄደውን የሰላም ጥረት እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በበኩላቸው÷በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አድንቀዋል።

የተጀመሩ ስራዎች በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጡ እምነታቸው መሆኑን መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.