Fana: At a Speed of Life!

በዘይት ገበያው ላይ ተጽእኖ እያሳረፉ ያሉ አስመጭዎችን መንግስት ሊቆጣጠር እንደሚገባ ነጋዴዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘይት ገበያው ላይ ተጽእኖ እያሳረፉ ያሉ አስመጭዎችን መንግስት በአግባቡ ሊቆጣጠር እንደሚገባ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ተናገሩ።

መንግስት ለባለሃብቶች መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲያስገቡ ቢፈቅድም ዋጋውን ማረጋጋት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

አስመጭዎቹ የምርት እጥረት ሳያጋጥማቸው የግል ጥቅማቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ገበያውን እንዳሻቸው እየዘወሩት ይገኛሉም ነው ያሉት።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጉዳዩን ለመመርመር ባደረገው ሙከራ ከአስመጭዎች ዘይትን ተረክበው ለችርቻሮ ነጋዴዎች የሚያቀርቡ ነጋዴዎች፥ አስመጭው ማን እንደሆነና በምን ያህል ዋጋ እንዳስመጡት ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው መመልከት ችሏል።

ጅምላ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች ይህ ከውጭ የሚገባ ዘይት በደላሎች አማካይነት እየቀረበላቸው እንደሆነም መታዘብ ተችሏል ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ስለምን ለጉዳዮ ትኩረት በመስጠት በቂ ቁጥጥር ማድረግ አልቻለም ሲልም ጠይቋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሃሰን መሃመድ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ መንግስት በዋጋው ላይ ጣልቃ እንዲገባ ያሳለፈው ውሳኔ ባለመኖሩ የዋጋውን ጉዳይ ለመወሰን አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል።

አያይዘውም በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ጣቢያችን በጉዳዮ ዙሪያ የሰራቸው ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ጉዳዮ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ ተቋማት ተገቢውን የቁጥጥርና ክትትል ስራ በየጊዜው ያስፈልጋል።

በዋጋ ትመና ላይ ጣልቃ ገብቶ ጣሪያ የነካውን የዋጋ ንረት በማረጋጋት ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ ጠንካራ ስራዎች መስራትም ከመንግስት ይጠበቃል።

በአወል አበራ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.