Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ ግንባታና መሬት ወረራ ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሐረሪ ክልል አስታውቋል፡፡
ክልሉ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ ከለውጡ በፊት ጀምሮ ተንሰራፍቶና ሥር ሰዶ የቆየ ቢሆንም የለውጥ ሂደቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀምና በአንዳአንድ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጭምር በመታገዝ ችግሩ ሲባባስ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
 
ይሁን እንጂ የክልሉ መንግስት ከህገ ወጥ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ የበለጠ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ባይኖረውም ችግሩ ለዓመታት ሲከማችና ሲወሳሰብ፣ መዋቅራዊ ሽፋንና ተሳትፎ እንደነበረው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
 
ለዚህም በእርምጃ አወሳሰድ ሂደቱ ያልተፈለገ የጸጥታና የውዝግብ፣ የማህበራዊ ቀውስ፣ የኢኮኖሚና ተያያዥ ችግሮችን እንዳያስከትል ጊዜ በመውሰድ የችግሩ ስፋትና ጥልቀትን ጨምሮ ህብረተሰቡን የሚያሳትፍ ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫና መወሰድ ያለበት ህጋዊ እርምጃ አንጥሮ የሚያወጣ ጥናትና ዝግጅት ሲያከናውን ቆይቷል ነው የተባለው።
 
በሐረሪ ክልል ባለው ውስን የቆዳ ሽፋን የተነሳ የገጠርና የከተማ መሬት ፍላጎትና አቅርቦት የተራራቀ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን÷ ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫና መወሰድ ያለበት ህጋዊ እርምጃ አንጥሮ የሚያወጣ ጥናትና ዝግጅት ሲያከናውን መቆየቱ ተመላክቷል፡፡
 
ይህ የመሬት ፍላጎትና አቅርቦት በፈጠረው ሰፊ ክፍተት እንዲሁም ቀደም ብሎ በነበረው የመንግስት አግባብ ያላቸው አካላት ለሙስና የተጋለጠ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ምክንያት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታን አማራጭ የችግራቸው ጊዜያዊ መፍትሄ አድርገውት መቆየቱም ተገልጿል፡፡
 
ከዚህ በከፋው መልኩ ደግሞ ጥቂት ስግብግብ ባለሀብቶች በመንግስት መዋቅር የተሰገሰጉ ሙሰኞችን በማሳተፍና የመሬት ደላሎችን በማሰማራት እጅግ ውስን በሆነውና በማይተካው የህዝብና የመንግስት የመሬት ሀብት ያልተገባ ጥቅም ሲያግበሰብሱ ቆይተዋል ነው የተባለው።
 
በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አግባብ ያላቸው አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መገባቱ ተነግሯል፡፡
በህገ ወጥ ግንባታና መሬት ወረራ ላይ የተጀመረው ይህ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የታከለበትና ህብረተሰቡን በንቃት ያሳተፈ እንደመሆኑ መጠን በተፈለገው ደረጃ ስኬታማ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
 
በቤት ችግር፣ ያልተገባ ጥቅም ለማካበትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ህገ ወጥ ግንባታ ያካሄዱና መሬት በመውረር አጥረው የያዙ የህብረተሰብ ክፍሎችም ድርጊታቸው ተገቢ እንዳልነበረ ከማመንና ከመጸጸት ባለፈ የገነቡትና ያጠሩትን በማፍረስ ተባባሪነታቸውንና ለህግ ተገዢነታቸውን በተግባር ሲያረጋግጡ ተስተውሏል ያለው መግለጫው÷ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የክልሉ መንግስት ልባዊ ምስጋናና አድናቆቱን ገልጿል።
 
የክልሉ መንግስት የጀመረው የማያዳግም እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ሌሎች ህገ ወጥ ግንባታ ያካሄዱ፣ የመንግስትና የህዝብ መሬት አጥራችሁ ያስቀመጣችሁ የህብረተሰብ ክፍሎችም አርአያነታቸውን በመከተል የንብረት ብክነትና ውድመት ሳይፈጠር በራሳችሁ ፍቃደኝነት ህገ ወጥ ግንባታቸውን፣ ንብረታቸውን እና አጥራችሁን በጥንቃቄ እንዲያነሱ ጥሪ ቀርቧል።
 
የክልሉ መንግስት ህገ ወጥ ግንባታ የተካሄደባቸውና በህገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች ታጥረው የተቀመጡ የገጠርና የከተማ መሬቶችን ወደመረጃ ቋት በማስገባት በፕላን ላይ ተመስርቶ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሃዊ ፣እኩል ተጠቃሚነት፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና ቁጠባን በሚያረጋግጥ ሂደት ለኢንቨስትመንትና ሰፊ የሥራ እድል ለሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለመንገድ፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለአረንጓዴ ልማትና ለመሳሰሉት ማህበራዊ ተቋማት ግንባታ እንደሚያውል አረጋግጧል።
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.